በዞኑ የ2018 ዓ.ም የ6ኛ እና 8ኛ ክፍል ከሰኔ ስምንት ጀምሮ የሚሰጠው ክልል አቀፍ ፈተና ሰላማዊ እና ከኩረጃ ነፃ በሆነ መንገድ እንዲጠናቀቅ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በቅንጅት መስራት እንዳለባቸው የጉራጌ ዞን ትምህርት መምሪያ ገለፀ

በዞኑ የ2018 ዓ.ም የ6ኛ እና 8ኛ ክፍል ከሰኔ ስምንት ጀምሮ የሚሰጠው ክልል አቀፍ ፈተና ሰላማዊ እና ከኩረጃ ነፃ በሆነ መንገድ እንዲጠናቀቅ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በቅንጅት መስራት እንዳለባቸው የጉራጌ ዞን ትምህርት መምሪያ ገለፀ

መምሪያው የ2018 ዓ.ም ክልል አቀፍ የ6ኛ እና 8ኛ ክፍል ፈተና አስተዳደር የኦረንቴሽን መድረክ በወልቂጤ ከተማ አካሂዷል።

የጉራጌ ዞን ትምህርት መምሪያ ሃላፊ አቶ መብራቴ ወልደማርያም እንደገለፁት፤ የመድረኩ አላማ በዞኑ 2018 ዓ.ም የ6ኛ እና 8ኛ ክፍል ከሰኔ ስምንት ጀምሮ በሚሰጠው ክልል አቀፍ ፈተና ፍፁም ሰላማዊ እና ከኩረጃ ነፃ በሆነ መንገድ እንዲጠናቀቅ ታሳቢ ያደረገ ነው።

በዞኑ ባለፉት 3 አመታት የ6ኛና 8ኛ ክፍል ክልል አቀፍ ፈተና በሰላማዊ መንገድ መስጠት እንደተቻለ ያስታወሱት አቶ መብራቴ፤ ይህንን ልምድ ይበልጥ በማጠናከር አሁንም ያለምንም የጸጥታ ችግር እንዲጠናቀቅ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ቅንጅት ወሳኝ ነው ብለዋል።

እንደጉራጌ ዞን 6ኛ ክፍል ከ18 ሺህ 4 መቶ በላይ እና ከ8ኛ ክፍል ከ19 ሺህ 8 መቶ በላይ ተማሪዎች የክልል አቀፍ ፈተና እንደሚወስዱ ነው አቶ መብራቴ ያስታወቁት።

ለዚህም ተማሪዎች የተዘጋጀውን ፈተና በአግባቡ እንዲፈተኑ የፈተና አስፈጻሚዎች፣ ሱፐርቫይዘሮች፣ የጣቢያ ኃላፊዎችና ከሌሎችም አካላት ጋር በመቀናጀት የቅድመ ዝግጅት ስራዎች መሰራታቸውን ገልፀዋል።

ፈተናው ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ የፀጥታ አካላት የተጠናከረ ስራ በመስራትና ትክክለኛ የመረጃ ልውውጥ ተግባር በማጠናከር ረገድ በትኩረት መስራት ይገባል በማለት አሳስበዋል።

የጉራጌ ዞን ሰላምና ጸጥታ መምሪያ ኃላፊ አቶ ነጋ አስፋ በበኩላቸው፤ የፊታችን ሰኔ ስምንት የሚሰጠው ክልል አቀፍ ፈተና ያለምን የጸታ ችግር እንዲጠናቀቅ በትኩረት እንደሚሰራ ገልጸዋል።

የዞኑ ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ተወካይ ምክትል ኮማንደር ገና ደገሙ፤ ፈተናውን በተማሪዎች እጅ እስከሚገባ የፈተናውን ደህንነት መጠበቅና ወደ መፈተኛ ጣበያዎች በባለቤትነት ማሰራጨት ይገባል በማለት አስገንዝበዋል።

በተጨማሪም ተማሪዎች ከተፈቀደላቸውን ከመፈተኛ ቁሳቁስ ውጭ ይዘው እንዳይገቡና ከሃሰተኛ ተባራሪ ጉዳዮች እንዲታቀቡ የክትትል ስራውን በትኩረት መስራት ይጠበቃል ሲሉም አቶ ነጋ ተናግረዋል፡፡ ።

የመድረኩ ተሳታፊዎች በበኩላቸው፤ ተማሪዎች የተዘጋጀውን ክልል አቀፍ ፈተና በተገቢው እንዲወስዱ በርካታ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል።

ለአብነትም ተማሪዎች በእውቀትም ሆነ በስነ ልቦና የማብቃት፣ ሎጅስቲክ የማሟላት፣ የግቢ ፅዳት እንዲሁም የመፈተኛ ክፍሎች የመደልደልና ሌሎችም መሰል ስራዎች ተሰርተዋል ሲሉም ጠቅሰዋል።

የተዘጋጀው ፈተና በየትምህርት ቤቶች ከማስራጨት አኳያ የነዳጅ አቅርቦት እጥረት መኖሩን ያነሱት አስተያየት ሰጪዎች ለዚህም ውጤታማነት ከማደያዎች ጋር በመናበብ አፋጣኝ መፍትሄ ሊሰጠው እንደሚገባም አመላክተዋል።

ዘጋቢ፡ እርካብነሽ ወልደማርቆስ – ከወልቂጤ ጣቢያችን