‎በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በደቡብ ኦሞ ዞን የ6ኛና 8ኛ ክፍል ክልላዊ ፈተና ለመስጠት በቂ ዝግጅት ማድረጉን የዞኑ ትምህርት መምሪያ አስታወቀ

‎በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በደቡብ ኦሞ ዞን የ6ኛና 8ኛ ክፍል ክልላዊ ፈተና ለመስጠት በቂ ዝግጅት ማድረጉን የዞኑ ትምህርት መምሪያ አስታወቀ

‎በዞኑም በበናፀማይ ወረዳ ተዘዋውረን ያነጋገራናቸው ተፈታኝ ተማሪዎችም የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

በበና ፀማይ ወረዳ የቀይ አፈር 1ኛ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ6ኛና 8ኛ ክፍል ክልላዊ ፈተና የሚፈትኑ ተማሪዎች በበኩላቸው ትምህርት ቤቱ ጥያቄዎችን በማውጣት፣ የማጠናከሪያና የማካካሻ ትምህርት በመስጠት ለፈተና እንድንዘጋጅ አድርጎናል ሲሉ አስተያየታቸውን ስጥተዋል።

‎የቀይ አፈር ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህርት ይሳለሙሽ ሽቱ፤ የማጠናከሪያ ትምህርትና ጥያቄዎችን በማዘጋጀት ተማሪዎች ጊዜያቸውን በአግባቡ እንዲጠቀሙ ማድረግና ለፈተናው እንዲዘጋጁ መደረጉን በማንሳት ባለፉት አመታት የታዩ የፈተና መጠነ ማለፉ ስብራቶችን ለማሻሻል ትምህርት ቤቱ በቂ ዝግጅት ማድረጉን ተናግረዋል።

‎የበና ፀማይ ወረዳ ትምህርት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አውኖ አርማኔ፤ በወረዳው በ6ኛ ክፍል ክልላዊ ፈተና ወንድ 425፣ ሴት 398 በድምሩ 823 ተማሪዎች ለፈተና የሚቀመጡ ሲሆን በ8ኛ ክፍል ክልላዊ ፈተና ደግሞ ወንድ 212 ሴት 144 በድምሩ 356 ተፈታኞች ለፈተና የሚቀመጡ መሆኑን አብራርተዋል።

‎የበና ፀማይ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪና የኮማንድ ፖስት ሰብሳቢ አቶ ዮሐንስ ጋርሾ፤ በሁለቱም የ6ኛና 8ኛ ክፍል በ8 የመፈተኛ አካባቢዎች የፈተና አስፈፃሚ ምልመላ፣ ድልድልና የፈተና አሰጣጥ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች መጠናቀቃቸውን በመግለጽ የፈተናው ሂደት በሠላም እንዲጠናቀቅ የወረዳው አስተዳደር በልዩ ትኩረት ቁጥጥር ያደርጋል ብለዋል።

‎የደቡብ ኦሞ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ መልካሙ ሺበሺ በበኩላቸው፤ ክልላዊ ፈተናዎቹ የተማሪዎችን የወደፊት የትምህርት ጉዞና ቀጣይ ተስፋ የሚወስኑ በመሆናቸው አፈጻጸሙ ፍጹም ፍትሃዊ፣ ግልጽና ካልተገባ አድልዎ የጸዳ መሆን እንደሚገባው በመግለጽ ባለድርሻ አካላት ኃላፊነታቸውን በተገቢው መንገድ እንዲወጡ ጠይቀዋል።

‎ተፈታኝ ተማሪዎችም በፈተና ወቅት በማናቸውም የሐሰት ወሬዎችና ውዥንብሮች ሳይደናገጡ፣ በተረጋጋ ስሜት የሚቀርብላቸውን ፈተና በራሳቸው ጥረት ለመስራት ዝግጁ መሆን እንዳለባቸውና ወላጆችና ትምህርት ቤቶችም የተፈታኞችን ሥነ-ልቦና ቀጣይነት ባለው መልኩ ከመገንባት አንጻር የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

‎ዘጋቢ፡ የሺእመቤት ዋሴ – ከጂንካ ጣቢያችን