ስርዓተ ትምህርቱ ሀገር በቀል ቅኝት እንዲኖረው ማድረግ የሀገራችንን አካባቢያዊ ጸጋዎች ለማልማትና ጥቅም ላይ ለማዋል ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ገለፀ

ስርዓተ ትምህርቱ ሀገር በቀል ቅኝት እንዲኖረው ማድረግ የሀገራችንን አካባቢያዊ ጸጋዎች ለማልማትና ጥቅም ላይ ለማዋል ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ገለፀ

የጉራጌ መልክአ ምድር መገለጫ የሆነው ጀፎረ በአለም ቅርስነት ማስመዝገብ ላይ ያተኮረ የማረጋገጫ ወርክሾፕ እና የርክክብ መርሃ ግብር በዩኒቨርስቲው ተካሂዷል።

የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ዶክተር አብድልሙህሲን ሀሰን እንደገለፁት፤ ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማር ባሻገር የአካባቢውን ማህበረሰብ ትኩረት ያደረገ የምርምርና የቴክኖሎጂ ሽግግር ተግባራት እያከናወነ ይገኛል።

ሀገር በቀል እውቀት ለዘመናዊ እውቀት መሠረት በመሆኑ ስርዓተ ትምህርቱ ሀገር በቀል ቅኝት እንዲኖረው ማድረግ የሀገራችንን አካባቢያዊ ጸጋዎች ለማልማትና ጥቅም ላይ ለማዋል ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።

ሀገር በቀል ዕውቀቶች ከዘመናዊ ጋር ተሳስረው እንዲቀጥሉ በጥናትና ምርምር እንዲዳብሩ ማድረግ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ድርሻ መሆኑን ገልፀዋል።

ዩኒቨርሲቲው ሀገር በቀል እውቀቶችን በማሰባሰብ፣ በመሰነድና በቴክኖሎጂ በመደገፍ ጥናትና ምርምር እያከናወነ መሆኑን ጠቅሰው በባህል ዘርፍ በጀፎሮ፣ በባህላዊ የዳኝነት ሥርዓት፣ አንትሮሽት አዳብና እቁብና በሌሎችም እሴቶች ላይ ጥናትና ምርምር ማካሄዱን ተናግረዋል።

ሀገር በቀል እውቀቶች ብሔራዊ ጥቅምና ሀገራዊ ፋይዳ እንዲኖራቸው ማድረግ ያስፈልጋል ያሉት ዶክተር አብዱልሙህሲን፤ የጉራጌ መልክአ ምድር መገለጫ የሆነው ጀፎረ በአለም ቅርስነት ለማስመዝገብ መሠራቱን አስረድተዋል።

የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዘዳንት ዶክተር ዮሐንስ ገብሬ በበኩላቸው፤ ጀፎረ ሁሉም ህዝብ በባለቤትነት የሚተላለፍበት፣ ክብቶች የሚቆዩበት ለቅሶ እና ማህበራዊ ጉዳዮች ሲገጥም ህዝቡ አንድ ላይ በመሰብሰብ ጉዳዩን በጋራ የሚፈጽምበት መሆኑን ገልፀው “የጀፎሮ ቂጫ” ወይም” የጀፎሮ ህግ” በመኖሩ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲሸጋገር ማድረጉን ተናግረዋል።

የጉራጌ ህዝብ እነዚህን እሴቶች በሀገር በቀል እውቀቱ ሲጠቀምባቸው መኖሩን ጠቁመው ጀፎረ ከጉራጌ ለዘመናዊ ዓለም የሚሰጥ ሕያው ሳይንስ መሆኑን ገልፀዋል። ይህን ቅርስ ጠብቆ ለቀጣዩ ትውልድ ማስተላለፍ የክልሉ፣ የዞኑ የህብረተሰቡና የዩኒቨርሲቲው የጋራ ብሔራዊ ኃላፊነት እንደሆነ አስገንዝበዋል።

የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትልና የባህል ዘርፍ ሀላፊ አቶ ደግነህ ቦጋለ፤ ጀፎረን በማልማት እና በመጠበቅ ወደ ትውልድ እንዲተላለፍ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ገልፀው በጥናትና ምርምር ለመንከባከብና በአለም ቅርስነት ለማስመዝገብ የተጀመረው ስራ መጠናከር አለበት ብለዋል።

ጀፎረን ጠብቆ ለቱሪዝም እድገት የሚሰጠውን አበርክቶ ማጎልበት እንደሚገባ ጠቁመው ባህል ታሪክና እሴቱን በመጠበቅ አንድነቱን ማጎልበት እንዳለበት ተናግረዋል።

በመርሀ ግብሩ የተገኙት ባለድርሻ አካላት በሰጡት አስተያየት ጀፎረ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሥርዓት የሚከናወንበት የጉራጌ ባህላዊ ጎዳናና የጉራጌ ማህበረሰብ ከጥንት ጀምሮ ያዳበረው የአኗኗር እሴቱ ነው።

ዩኒቨርሲቲው በጥናትና ምርምር በመጠበቅ በአለም ቅርስነት እንዲመዘገብ የተጀመረው ስራ ጀፎረ የበለጠ ለማስተዋወቅና ለትውልድ ለማስተላለፍ እንደሚረዳ ተናግረዋል።

ባህል፣ እውቀትና ቅርስ ጉራጌ ሀብ (Gurage Hub, Cross- Platform System for Gurage Cultures and Values” የተሰኘው ቴክኖሎጂ እና የጉራጌ ማህበረሰብ መገለጫ የሆነውን ጀፎረ ላይ ጥናቶች ቀርበዋል።

በመድረኩ የሁለቱ ጉራጌ ዞን አመራሮች፣ የዩኒቨርሲቲው ተመራማሪዎችና የሀገር ሽማግሌዎች የተገኙ ሲሆን የጥናትና ምርምሩ ሰነድ ለሁለቱም ጉራጌ ዞኖች ርክክብ ተደርጓል።

ዘጋቢ፡ ሄኖክ ተክሌ – ከወልቂጤ ጣቢያችን