48 ሀገራት፣ 104 ጨዋታዎች እና አዲስ ጅማሮ በ2026 የዓለም ዋንጫ
በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ 48 ሀገራት የሚሳተፉበት እና በአሜሪካ፣ ካናዳ እና ሜክሲኮ ጣምራ አዘጋጅነት የሚካሄደው 23ኛው የፊፋ የዓለም ዋንጫ ዛሬ በይፋ ይጀመራል።
የውድድሩ የመክፈቻ ጨዋታ አስተናጋጇ ሜክሲኮ ከደቡብ አፍሪካ ጋር በዋና ከተማዋ ሜክሲኮ ሲቲ በሚገኘው ታሪካዊው ‘አዝቴካ ስታዲየም’ ምሽት 4 ሰዓት ላይ ይካሄዳል።
በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሳታፊ ሀገራት ቁጥር ወደ 48 ከፍ ብሏል።በውድድሩ በድምሩ 104 ጨዋታዎች ይደረጋሉ።
ሀገራቱ በ12 ምድቦች ተከፍለው የሚወዳደሩ ሲሆን፣ ውድድሩ በ16 አስተናጋጅ ከተሞች እና በ16 ስታዲየሞች ይካሄዳል።
የዘንድሮው የዓለም ዋንጫ እስከ ሐምሌ 12 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ የሚቆይ ይሆናል።
በዓለም ዋንጫ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በሶስቱም አስተናጋጅ አገራት የተለያዩ የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓቶች ይከናወናሉ።
የዛሬው የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ጨዋታው ከመጀመሩ 90 ደቂቃ አስቀድሞ የሚጀመር ሲሆን፣ ሻኪራ እና ቡርና ቦይ የውድድሩን ይፋዊ መዝሙር “Dai Dai” ያቀርባሉ።
በቀጣዮቹ ቀናት በቶሮንቶ (ካናዳ) እና በሎስ አንጀለስ (አሜሪካ) ተጨማሪ የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓቶች የሚከናወኑ ሲሆን፣ እንደ ኬቲ ፔሪ፣ ፊውቸር፣ ሊሳ፣ ሬማ፣ አሌሃንድሮ ፌርናንዴዝ፣ ጄ ባልቪን እና ሌሎችም ዓለም አቀፍ ድምጻውያን ስራዎቻቸውን ያቀርባሉ።
የዘንድሮው የዓለም ዋንጫ በፋይናንስ ረገድም በታሪክ ትልቁ ሆኖ ተመዝግቧል። ፊፋ ለተሳታፊ ሀገራት የሚያቀርበውን አጠቃላይ የፋይናንስ አስተዋጽኦ 871 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር አድርሶታል። ከዚህ ውስጥ 655 ሚሊዮን ዶላሩ በቀጥታ ለሽልማት የሚውል ሲሆን፣ ይህም በኳታሩ 22ኛው የዓለም ዋንጫ የነበረውን የሽልማት መጠን በ50 በመቶ ብልጫ አለው።
የዘንድሮው የዓለም ዋንጫ ከዚህ ቀደም ከነበሩት በላቀ መልኩ የዘመናዊ ቴክኖሎጂ ውጤቶች የሚታዩበት ይሆናል።
ይበልጥ የጠራ እና ፈጣን የሆነ የኦፍሳይድ ውሳኔዎችን ለመስጠት የሚያስችል የተሻሻለ የቴክኖሎጂ ስርዓት በሁሉም ጨዋታዎች ላይ ጥቅም ላይ ይውላል።
በሜዳ ላይ የሚከናወኑ አወዛጋቢ ውሳኔዎችን ለመቀነስ የቪዲዮ ረዳት ዳኞች (VAR) በሰፊው አገልግሎት ላይ የሚውሉ ሲሆን፣ በዘንድሮው ውድድር ውሳኔዎችን ለተመልካቾች በግልጽ የማብራራት ሂደት ይተገበራል።
ውድድሩን በአካል መታደም የማይችሉ ደጋፊዎች በዓለም ዙሪያ በሚገኙ ትላልቅ ከተሞች በተዘጋጁ “Fan Zones” አማካኝነት ጨዋታዎቹን በጋራ መመልከት ይችላሉ።
በ16ቱ አስተናጋጅ ከተሞች ውስጥ ደጋፊዎች የጨዋታውን ድባብ እንዲጋሩ የሚያደርጉ ልዩ የደጋፊዎች ማዘውተሪያ ስፍራዎች ተዘጋጅተዋል።
48 ሀገራት በ12 ምድብ (ምድብ A እስከ L) ተከፍለዋል። ከእያንዳንዱ ምድብ አሸናፊዎች እና ሁለተኛ የወጡት እንዲሁም ምርጥ ሶስተኛ ደረጃን የያዙ ሀገራት ወደ ጥሎ ማለፍ (32ቱ ውስጥ) ያልፋሉ።
ይህ አዲስ አሰራር በውድድሩ ላይ ያለውን የፉክክር ድባብ ከፍ እንደሚያደርገው ይጠበቃል።
ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ

More Stories
በክልሉ ለሚገኙ የባህል ፍርድ ቤት ሽማግሌዎች የተዘጋጀ ስልጠና እየተሰጠ ነው
ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በይርጋጨፌ ከተማ ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ የተገነቡ የተለያዩ የልማት ስራዎችን መርቀው ከፈቱ
ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ የዲላ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መርቀው ከፈቱ