የአካባቢ ብክለትን እና የካርበን ልቀትን ከመከላከል ባሻገር ለታዳሽ ሀይል ትኩረት ሊደረግ ይገባል – የክልሉ አካባቢ ጥበቃና አየር ንብረት ለውጥ ባለስልጣን
ሀዋሳ፡ ግንቦት 29/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) የአካባቢ ብክለትን እና የካርበን ልቀትን ከመከላከል ባሻገር ለታዳሽ ሀይል ትኩረት ሊደረግ እንደሚገባ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አካባቢ ጥበቃና አየር ንብረት ለውጥ ባለስልጣን አስታወቀ፡፡
የዓለም አካባቢ ቀን በክልሉ በሁሉም አካባቢዎች “የአየር ንብረት እርምጃ፣ ለዛሬ ህይወታችን፣ ለነገ ትውልዳችን” በሚል መሪ ቃል እየተከበረ እንደሚገኝም ተገልጿል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አካባቢ ጥበቃና አየር ንብረት ለውጥ ባለስልጣን የዓለም አካባቢ ቀንን በማስመልከት ለሚዲያ መግለጫ ሰጥቷል።
የዓለም አካባቢ ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ 53ኛ፣ በኢትዮጵያ ለ33ኛ፣ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ደግሞ ለ 3ኛ ጊዜ እየተከበረ ይገኛል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አካባቢ ጥበቃና አየር ንብረት ለውጥ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ግዛቴ ግጄ፤ በዓሉ በተለያዩ ተቋማት ስለ አካባቢ እና የአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ ግንዛቤ ለመፍጠርና ምድርን ከብክለት ለመታደግ በማለም እንደሚከበር አብራርተዋል።
የደን፣ የውሀ ሀብታችንንና ረግረጋማ አካባቢዎችን ለመጠበቅ ሁሉም ሀላፊነቱን መወጣት እንዳለበት አሳስበው፤ ወንዞቻችንና ሀይቆቻችን ከመጠበቅ ባሻገር ብከለትን የሚፀየፍ ማህበረሰብ ለመፍጠር በማሰብ በዓሉ እንደሚከበርም አክለዋል።
የአካባቢ ብክለትን እና የካርበን ልቀትን ከመከላከል ባሻገር ታዳሽ ሀይልን መጠቀም ላይ ሁሉም ወደ እርምጃ መግባት አለበት ያሉት አቶ ግዛቴ፤ ቆሻሻን የሚፀየፍ ማህበረሰብ ለመፍጠር እየተከናወነ የሚገኘውን እንቅስቃሴ አጠናክሮ ማስቀጠል ያሻል።
የአካባቢ አጀንዳ የሁሉም አጀንዳ መሆን እንዳለበት ያሳሰቡት ዳይሬክተሩ፤ የትውልዱን ህይወት ጠባቂና ጠበቃ መሆን ይገባል ሲሉም አሳስበዋል።
ተፈጥሮን ከመንከባከብ ባሻገር ዘላቂ መፍትሔ ላይ በመስራት የተጠበቀችና የፀዳች ኢትዮጵያን ለትውልዱ ለማውረስ መንግስት በአካባቢ ጥበቃና በታዳሽ ሀይል ላይ እየሰራ ይገኛልም ብለዋል።
በከተሞች የሚስተዋለው የቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ ስርዓት ሊዘምን እንደሚገባ ያሳሰቡት አቶ ግዛቴ፤ የኘላስቲክ ቆሻሻ አያያዝ ላይ እየተወሰደ የሚገኘው እርምጃ ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።
በክልሉ በየዓመቱ ጎርፍ፣ የመሬት መንሸራተትና ናዳ ተከስቶ ውድመት ማድረሱ የአየር ንብረት ለውጥ ዳፋ መሆኑን አውስተው፤ ብዝሀ ህይወትን ጠብቆ ማቆየት ለነገ የሚባል አለመሆኑን አሳስበዋል።
ፅዱ ኢትዮጵያን እውን በማድረግ በአካባቢ ብክለት ምክንያት የሚከሰተውን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ የጤና ጉዳትና አደጋን በመከላከልና በመጠበቅ ዜጋ ተኮር ስራን መስራት አስፈላጊ መሆኑን ኃላፊው አብራርተዋል።
ፅዱ ኢትዮጵያን ለመፍጠር የተጀመሩ የኮሪደር እና የወንዝ ዳር ልማትን ማፋጠንና ማስፋፋት አስፈላጊ መሆኑን ገልፀው፤ ባለድርሻ አካላት ለዘርፉ ትኩረት በመስጠት አካባቢን ከብክለት ሊታደጉ ይገባል ብለዋል።
ዘጋቢ፡ ተመኙህ ገረሱ – ከአርባምንጭ ጣቢያችን

More Stories
በዩኒቨርሲቲው በምርምር እና በቴክኖሎጂ ሽግግር ዘርፍ እየተከናወኑ የሚገኙ ተግባራት ከጊዜ ወደ ጊዜ ውጤታማ እየሆኑ መምጣታቸው ተገለፀ
7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሕብረተሰቡ በነፃነት ተሳትፎ ያደረገበት መሆኑ ተገለጸ
ጋዜጣዊ መግለጫ