በዩኒቨርሲቲው በምርምር እና በቴክኖሎጂ ሽግግር ዘርፍ እየተከናወኑ የሚገኙ ተግባራት ከጊዜ ወደ ጊዜ ውጤታማ እየሆኑ መምጣታቸው ተገለፀ

በዩኒቨርሲቲው በምርምር እና በቴክኖሎጂ ሽግግር ዘርፍ እየተከናወኑ የሚገኙ ተግባራት ከጊዜ ወደ ጊዜ ውጤታማ እየሆኑ መምጣታቸው ተገለፀ

‎በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅነት “በጥንካሬ በመቋቋም ወደ ዘላቂ ዕድገት ለመሻገር የሚረዱ መዋቅራዊ የለውጥ መንገዶች” በሚል መርህ 2ኛው ዓለም አቀፍ የምርምር ኮንፍረንስ ተካሂዷል።

የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት አብዱልሙህሲን ሀሰን(ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት፤
ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ከተቋቋሙበት አላማ አንዱ የምርምር ስራዎች ማከናወን ነው።

በምርምር ዘርፍ ለማከናወን የሚታቀዱ ተግባራት አለም አቀፋዊ ይዘት መጠበቅ አለባቸው ያሉት ተጠባባቂ ፕሬዝደንቱ መሰል አለም አቀፍ ኮንፈረንሶች መካሄዳቸው ደግሞ ይህ ዓላማ ከግብ እንዲደርስ ያስችላሉ ሲሉ ተናግረዋል።

በመሆኑም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የመማር ማስተማር፣ የማህበረሰብ አገልግሎት እና ችግር ፈቺ የጥናትና ምርምር ስራዎችን ታሳቢ በማድረግ አለም አቀፋዊነት ይዘት ያላቸው ተግባራት እያከናወኑ ይገኛሉ ሲሉም አክለዋል።

ዩኒቨርሲቲው በየጊዜው በሚያካሂዳቸው ኮንፈረንሶች በርካታ የጥናትና ምርምር ስራዎች እንደሚቀርቡ ያነሱት ተጠባባቂ ፕሬዝደንቱ፤ ኮንፈረንሱ የምርምር ስራዎች ውጤታማ ለማድረግ፣ ተመራማሪዎች ልምድ እንዲለዋወጡ ለማስቻልና በአለም አቀፍ ደረጃ የሚካሄዱ የጥናትና ምርምር ስራዎች በሀገሪቱ ከሚከናወኑ የምርምር ስራዎች ውጤት ጋር ያላቸውን ቁርኝት ለመለየት ያግዛል ብለዋል።

የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ዮሀንስ ገብሩ (ዶ/ር) በበኩላቸው በዩኒቨርሲቲው በምርምር እና በቴክኖሎጂ ሽግግር ዘርፍ እየተከናወኑ የሚገኙ ተግባራት ከጊዜ ወደ ጊዜ ውጤታማ እየሆኑ መምጣታቸውን ገልፀዋል።

በኮንፍረንሱ ላይ 19 ምርምሮች የቀረቡ ሲሆን ከ5 አለም አቀፍ ዩኒቨርሲቲዎች 7 ጥናታዊ ጽሑፎች፣ ከሌሎች የሀገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች 5 እንዲሁም ከወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ 7 ጥናታዊ ፅሁፎች መቅረባቸውንም አሰረድተዋል።

ይህም ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ አያከናወናቸው የሚገኙ ስራዎች ይበልጥ ለማስተዋወቅ እንደሚያስችል ዶ/ር ዮሀንስ ገልፀዋል።

ከኮንፈረንሱ ተሳታፊዎችና የምርምር ስራዎቻቸውን ካቀረቡ ተመራማሪዎች መካከል በሰጡት አስተያየት በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት ተመራማሪዎች የቀረቡ የምርምር ስራ ውጤቶች የማህበረሰቡን ችግር የሚቀርፉ እንደሆኑ ገልፀዋል።

ኮንፈረንሱ ፋይዳው ከፍተኛ ነው ያሉት አስተያየት ሰጪዎቹ በተለይም እርስ በርስ የልምድ ልውውጥ ያደረጉበት መሆኑንም አመላክተዋል።

ዩኒቨርሲቲዎች የማህበረሰቡን ችግር የሚፈቱ፣ ለፖሊሲ አውጪዎች ግብአት የሚሆኑና የሃገርን ልማት የሚያፋጥኑ የጥናትና ምርምር ውጤቶችን ከጠረጴዛ መቀመጥ ባሻገር ተግባር ላይ እንዲውሉ የሁሉም ባለድርሻ አካላት የተጠናከረ እግዛ ይሻልም ብለዋል።

ዘጋቢ፣ ሚፍታ ጀማል – ከመልቂጤ ጣቢያችን