7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሕብረተሰቡ በነፃነት ተሳትፎ ያደረገበት መሆኑ ተገለጸ
ምርጫው ሠላማዊና ዲሞክራሲያዊ ሆኖ መጠናቀቁን መነሻ በማድረግ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የሸካ ዞን የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በማሻ ከተማ ውይይት አካሂዷል።
ምርጫው ስኬታማ እንዲሆን አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላትም ምስጋና አቅርቧል።
በጋራ ምክር ቤቱ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በሰላም ስኬታማ ሆኖ መጠናቀቁ በሀገሪቱ የፖለቲካ ምህዳር መስፋቱን የሚያመላክት መሆኑ ተነስቷል።
የሸካ ዞን የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ አስማማው አለሙ፤ የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሂደት ዉጤታማና ለቀጣይ ተሞክሮ የተወሰደበት እንደሆነ ተናግረዋል።
ከቅድመ ዝግጅት ጀምሮ የጋራ ምክር ቤቱ ምርጫው ሠላማዊ፣ ዲሞክራሲያዊና ሁሉን አሳታፊ እንዲሆን በተደረገው ጥረት የተሻለ ስራ መሰራቱን ገልጸው ይህ ደግሞ በንግግር የሚያምን ትውልድ መፈጠሩን የሚያመለክት ስለመሆኑም ሰብሳቢው በአፅንኦት አንስተዋል።
የሸካ ዞን የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ምክትል ሰብሳቢ አቶ አለማየሁ አለሙ በበኩላቸው፤ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ከዚህ ቀደም ከነበሩ የምርጫ ሂደቶች ሕብረተሰቡ በነፃነት ተሳትፎ ያደረገበት መሆኑን ተናግረዋል።
የጋራ ምክር ቤቱ የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሠላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ መንግስት ያስቀመጣቸውን የህግ ማዕቀፎች በመከተል የዴሞክራሲ ምህዳሩን ማስፋት የተቻለበት እና በፉክክሩም የትብብር ሚዛን እንዲጠብቅ ማድረግ የተቻለበት መሆኑን ገልፀው ይህን ልምድ ማዳበር ይገባል ብለዋል።
አሁን ላይ የተጀመሩ የዲሞክራሲ ግንባታ ስራዎች በቀጣይም በተሻለ ተቋማዊ ጥንካሬ ማስቀጠል እንደሚገባም ምክትል ሰብሳቢው ጠቁመዋል።
በምርጫዉ ዕለት በዞኑ በሚገኙ ሁሉም የምርጫ ጣቢያዎች ላይ ከንጋቱ 12 ሰዓት እስከ ምሽት ድረስ ህብረተሰቡ ለፈለገው የፖለቲካ ፓርቲ ያለማንም ተጽዕኖ ድምፅ መስጠት እንደቻለም በጋራ ምክር ቤቱ ውይይት ላይ ተገልጿል።
ለስኬታማነቱ ደግሞ የህዝቡ ሚና የጎላ በመሆኑ እውቅና መስጠት እንደሚገባም ተጠቁሟል።
በተለይ በየደረጃው የሚገኙ የጸጥታ መዋቅር የጎላ አስተዋጽኦ ማበርከት መቻላቸውም የተገለፀ ሲሆን ይህም እስከ ድህረ ምርጫ ድረስ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ተብሏል።
የምርጫ ውጤት ምንም ሆነ ምን የሁሉም ፓርቲዎች ትግል ኢትዮጵያን ማሻገር ብቻ በመሆኑ በድህረ ምርጫ ወቅት የምርጫ ቦርዱን ህግ ማክበርና ማስከበር ላይ ሁሉም ፓርቲ ለአመራሮቹ፣ ለአባላቱና ለደጋፊው ስለድህረ ምርጫ ግንዛቤን የማስጨበጥ ስራን ማጠናከር እንደሚገባም በአጽንኦት ተነስቷል።
የመንግስት መዋቅር ደግሞ የመሪነት ሚናውን በአግባቡ መወጣት እንደሚጠበቅበት የተገለጸ ሲሆን በተለይ የመራጩን ህዝብ ስነልቦናን መጠበቅ ላይ ትኩረት እንዲደረግም አስተያየት ተሰጥቷል።
በድህረ ምርጫ ወቅት የዴሞክራሲ ስርአት የሚፈተንበት በመሆኑ ሁሉም ነገር በጥንቃቄ መምራት እንደሚባ የተገለፀ ሲሆን መንግስት ለመመስረት የሚያስችል ድምፅ የሚያገኘዉ አንድ ፓርቲ ቢሆንም በጥቅሉ አሸናፊ ኢትዮጵያ እንደሆነችና እንዲሁም የህዝቡን ድምጽ ማክበር ላይ ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባም ተነስቷል።
የዞኑን መንግስት ጨምሮ አጠቃላይ የምርጫው ሂደት ሰላማዊና የተሳካ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ሚናቸውን ለተወጡ ሁሉ ምስጋና ያቀረበው የጋራ ምክር ቤቱ፤ ውጤቱ እስኪገለጽ ድረስ የምርጫ ቦርድ ህግ እንዲከበር ብርቱ ስራ ከሁሉም የፖለቲካ ፓርቲ እንደሚጠበቅ የጋራ ምክር ቤቱ አቅጣጫ አስቀምጧል።
ዘጋቢ: ታሪኩ ታደሰ – ከማሻ ጣቢያችን

More Stories
በዩኒቨርሲቲው በምርምር እና በቴክኖሎጂ ሽግግር ዘርፍ እየተከናወኑ የሚገኙ ተግባራት ከጊዜ ወደ ጊዜ ውጤታማ እየሆኑ መምጣታቸው ተገለፀ
ጋዜጣዊ መግለጫ
በዘንድሮ የትምህርት ዘመን የተማዎችን ውጤት ለማሻሻል በተደረገው ጥረት የተሻለ ውጤት እንደሚጠበቅ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ትምህርት ቢሮ ገለፀ