የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ውሃ፣ መስኖና ማዕድን ልማት ቢሮ በዋን ዋሽ ፕሮግራም አማካኝነት ከ1 መቶ 15 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ 4 የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ግንባታ ለማከናወን የውል ስምምነት ተፈራረመ
ፕሮጀከቶቹ ሲጠናቀቁ ከ58 ሺ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርጉ ተመላክቷል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ውሃ፣ መስኖና ማዕድን ልማት ቢሮ ሃላፊ አቶ ዳዊት ሃይሉ ዋን ዋሽ ፕሮግራም ትልቁ ተልዕኮው በውሃ፣ ጤናና ትምህርት ላይ እንደሆነ ገልፀው ይህም ለማህበረሰቡ የጤና መሠረት እንዲሁም የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ ፋይዳው የጎላ እንደሆነም አስረድተዋል።
ዋን ዋሽ በቀድሞ ደቡብ ክልል እና በአዲሱ ማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልልን ጨምሮ ለበርካታ አመታት የቆየ ፕሮጀክት ሲሆን በገጠር አካባቢ ለሚኖሩ የማህበረሰብ ክፍሎች ትልቅ እገዛና እፎይታ በመስጠት በርካታ አመርቂ ውጤቶች ተመዝግበዋል ሲሉ አቶ ዳዊት ተናግረዋል።
አክለውም ዋን ዋሽ ፕሮግራም በማጠናቀቂያና በተጨማሪ የጊዜ ገደብ ውስጥ እንደሚገኝና በዚህ ማጠናቀቂያ ወቅት ላይ 4 የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ግንባታ ለማከናወን የውል ስምምነት መግባቱን ተናግረው በዚህም ፕሮጀክቶቹን በአጭር ጊዜ ውስጥ በጥራትና በፍጥነት ማጠናቀቅ እንደሚገባ አመላክተዋል።
በክልሉ ሳጃ ከተማ ፣ አበጀ ፣ ጨቦና ኮምበል የሚገነቡት እነዚህ የውሃ ፕሮጀክቶች ከ1 መቶ 15 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የሚደርግባቸው መሆኑንና በዚህም ከ58 ሺ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርጉም ተገልጿል።
አሁን ካለው አለም አቀፍና ሃገር አቀፍ የነዳጅ እጥረት ምክንያት ለተቋራጮች የስራ እክል እንዳይሆን ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመነጋገር አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል ይደረጋል ብለዋል።
የሚገነቡት የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶቹ በእያንዳንዱ ማህበረሰብ ክፍል ላይ ለውጥ የሚያመጡ መሆናቸውን በመገንዘብ ግንባታዎቹ በሚከናወንባቸው አካባቢዎች የሚገኙ የአስተዳደር ሃላፊዎችና የህብረተሰብ ክፍሎች ትብብር እንዲያደርጉ አቶ ዳዊት ጥሪ አቅርበዋል።
የአሚናዳብ ኮንስትራክሽንና ትሬዲንግ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ሙሉጌታ ኪዳኔ እና የቢንያም ሻምበል ህንፃና ውሃ ስራዎች ተቋራጭ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ቢንያም ሻምበል በበኩላቸው አስፈላጊውን የሰው ሃይልና ማሽን በሟሟላት ፕሮጀክቶቹን በፍጥነትና በጥራት ማጠናቀቅ የሚያስችል ዝግጅት ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
ዘጋቢ፡ ፍስሃ ክፍሌ

More Stories
በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመታገዝ በዝንጅብል ምርት የተሰማሩ አርሶ አደሮች ተጠቃሚ መሆናቸውን ገለፁ
ምርጫው ነጻ ፍትሀዊ እና ሰላማዊ ሆኖ መጠናቀቁን በቤንች ሸኮ ዞን በሚዛን ተፈሪ የምርጫ ክልል የሚገኙ የሲቪክ ማህበራትና የፖለቲካ ፓርቲ ታዛቢዎች ተናገሩ
በሸካ ዞን የሚገኙ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የተሻለ ዴሞክራሲያዊ አሠራር የታየበት ስለመሆኑ ተናገሩ