ማህበረሰቡ የምርጫውን እለት በመዘንጋት የመምረጥ እድሉን እንዳያሳልፍ ግንዛቤ የመፍጠር ስራ በሆሳዕና ከተማ እየተሰራ ነው

ማህበረሰቡ የምርጫውን እለት በመዘንጋት የመምረጥ እድሉን እንዳያሳልፍ ግንዛቤ የመፍጠር ስራ በሆሳዕና ከተማ እየተሰራ ነው

ሀዋሳ፡ ግንቦት 23/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) የምርጫ ሂደቱ የተሳካ እንዲሆን በበጎ ፈቃደኝነት ስለ ምርጫ ሂደት ግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርቶችን እየሰጡ መሆኑን የሆሳዕና ከተማ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ገለፁ።

ወጣቶቹ ከዚህ በፊት ማህበረሰቡ የምርጭ ካርድ በመውሰድ ለምርጫ ዝግጅት እንዲያደርግ ቅስቀሳ ሲያደርጉ መቆየታቸውንም ተናግረዋል።

ከበጎ ፈቃደኛ ወጣቶቹ መካከል ወጣት ፀጋነሽ አለሙ እሷ እና መሰል ጓደኞቿ በከተማዋ የተለያዩ ቦታዎች በመዘዋወር ማህበረሰቡ የወሰደውን ካርድ በመጠቀም የምርጫ ሂደቱን ሳያውክ ሰላማዊ በሆነ መንገድ እንዲመርጥ የሚያስችሉትን ግንዛቤዎች እየሰጠን እንገኛለን ስትል እየሰሩ ስለሚገኙት የጎዳና ላይ ግንዛቤ የመስጠት ስራ አስረድታለች።

ወጣት ሚሊዮን አማረ በበኩሉ፤ ወጣቱ በበጎ ፈቃደኝነት ለሀገር ሰላም እና የምርጫውን ሂደት ሊያስተጓጉሉ በሚችሉ ጉዳዮች ላይ ግንዛቤ መስጠት መቻሉ የሚበረታታ ተግባር መሆኑን አፅንኦት ሰቶበታል።

ወጣቶች በሁሉም መስክ በመሳተፍ ለሀገራቸው ከፍታ የድርሻቸውን መወጣት ዜጋዊ ግዴታቸው ነው ያለው ወጣቱ፤ ምርጫ ደግሞ ከሌሎች ጊዜያት በበለጠ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ በመሆኑ ግንዛቤ የማስጨበጥ ተግባሩ በሁሉም ክልል ከተሞች ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ሲል መልዕቱን አስተላልፏል።

በነገው እለት የሚካሄደው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በተሳካ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ አጠቃላይ የኢትዮጵያ ህዝብ በእለቱ የሚጠበቅበትን በማድረግ ዜጋዊ ሀላፊነቱን ሊወጣ ይገባል ያሉት ደግሞ በስፍራው ተገኝተው የግንዛቤ ማስጨበጫ ሂደቱን የተከታተሉ መንገደኞች ናቸው።

ዘጋቢ፡ ሸዊት ሂርጶ