በክልሉ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ የተጀመሩ ተግባራት ተጠናክረው መቀጠል አለባቸዉ – ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ

በክልሉ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ የተጀመሩ ተግባራት ተጠናክረው መቀጠል አለባቸዉ – ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ

ሀዋሳ፡ ሐምሌ 06/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) በክልሉ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ የተጀመሩ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ ገለጹ፡፡

በክልሉ የ2018 የክረምት ወራት የትምህርት ተግባራት የንቅናቄ መድረክ በሳውላ ከተማ ተካሂዷል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ባስተላለፉት መልዕክት፥ ሀገር የምትበለጽገው በትምህርት ዘርፍ የተሻለ ስራ ሲሰራ መሆኑን ጠቁመው፥ ዘርፉ በተቀናጀ መንገድ ከተመራ የሚፈለገው ውጤት ይመዘገባል ብለዋል፡፡

ትምህርት ቤቶችን የማዘመን ስራ በዘመቻ መልክ መተግበር እንዳለበት የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ ትምህርት ቤቶችን ለመማር ማስተማር ስራ ምቹ የማድረግና ግብዓት የማሟላት ተግባር በማጠናከር ሊሰራ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

በትምህርት ጥራት ላይ ውጤት እየተመዘገበ መምጣቱን ጠቁመው፥ ይህንኑ የማጠናከር ስራ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል።

በዘንድሮው የክረምት ወቅት ከሚከናወኑ ተግባራት የትምህርት ዘርፍ ቀዳሚ አጀንዳ መሆን እንዳለበት የገለፁት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድሩ፥ ለሚፈለገው ውጤት የትምህርት ቤቶች ግብዓት በተገቢ መንገድ ማሟላት እንደሚያስፈልግ አጽንኦት ሰጥተዋል።

የመምህራን አቅም በማጎልበት የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ የተጀመሩ ተግባራት እንደሚጠናከሩ ርዕሰ መስተዳድሩ አስገንዝበዋል።

ህዝቡ የሚፈለገውን ውጤት ለማስመዝገብ እንዲቻል በ7ተኛው ጠቅላላ ምርጫ ያሳየውን ተግባር በትምህርት ላይም በመድገም ሀገራዊ ኃላፊነት እንዲወጣ ርዕሰ መስተዳድሩ ጥሪ አቅርበዋል ።

የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዮት ደምሴ ሀገር የምታድገው በእውቀትና በስነምግባር የታነፀ ዜጋ ሲፈጠር ብቻ ነው ብለዋል።

ትምህርት ትውልድን ለመቅረጽ ከፍተኛ ድርሻ እንደሚኖረው የገለፁት አቶ አብዮት በክልሉ የትምህርት ጥራትና ፍትሃዊነት እንዲረጋገጥ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል።

በክልሉ የ2018 ዓ.ም አፈፃፀምና የቀጣዩን አመት ዕቅድ መነሻ በማድረግ በቀረበው ሪፖርት ላይ የመድረኩ ተሳታፊዎች ውይይት አካሂደዋል።

በመድረኩ ከርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በተጨማሪ የክልሉ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊች የሥራ መመሪያዎችንና ማብራሪያዎችን ሠጥተዋል።

ዘጋቢ፡ አወል ከድር – ከሳውላ ጣቢያችን