”ምርጫው በሠላም እንዲጠናቀቅ አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል” – የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን
ሀዋሳ: ግንቦት 22/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) ምርጫው ሠላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ፍስሃ ጋረደው ገለጹ።
የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ፍስሃ ጋረደው፥ ፖሊስ ከቅድመ ምርጫ ወቅት ጀምሮ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት ምርጫው ሠላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ እየተሰራ ነው ብለዋል።
ክልሉ ለማደግ የሚተጉ ሕዝቦች ያሉበት ሰላማዊ ክልል መሆኑን አንስተው፥ ሂደቱ ፍጹም ሠላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ከፀጥታ አካላት ጋር በመተባበር እየተንቀሳቀሱ ስለመሆኑ ጠቅሰዋል።
ተፎካካሪ ፓርቲዎች የመንግሥት ሥልጣንን ለመያዝ በሚያደርጉት ሠላማዊ ትግል ከቅስቀሳ ወቅት ጀምሮ የሕዝቡን መብት ባከበረ መልኩ እንዲንቀሳቀሱ ሲደረግ መቆየቱን አንስተዋል።
ለምርጫ ጣቢያዎች የምርጫ ቁሳቁስ የማድረስ ሥራ እየተከናወነ ነው ያሉት ኮሚሽነሩ በእስካሁኑ ሂደት ምንም ዓይነት ችግር አለማጋጠሙን ገልፀዋል።
ፓሊስ ምርጫውን ሠላማዊ ሆኖ እንዳይጠናቀቅ የሚንቀሳቀሱ ጸረ ሠላም ኃይሎችን በመከታተል እርምጃ መውሰድ የሚያስችል ዝግጅት መደረጉን ገልፀው፤ ከአድማ ብተና ሠራዊት ጀምሮ በየደረጃው ያሉ አባላት ዝግጁ መሆናቸውን አመላክተዋል።
ከዚህም ባለፈ የፌደራል መንግሥት የሚያስተዳድራቸው ክልሉን አቋርጠው የሚያልፉ መንገዶችን በመጠበቅ ሠላማዊ ሆነው እንዲዘልቁ እየተደረገ ነው ብለዋል።
ፖሊስ የምርጫ አስፈፃሚዎችን፣ መራጮች እና የምርጫ ቁሳቁስ ደህንነት በመጠበቅ በክልሉ የሚገኙ ከሦስት ሺህ በላይ ምርጫ ጣቢያዎች ሠላማዊ ሆነው እንዲጠናቀቅ ግብረ-ኃይል ተቋቁሞ እየተሰራ ነው ብለዋል።
ግብረ-ኃይሉ ምርጫው ተጠናቆ ውጤት ይፋ እስኪደረግ ሥራውን በተቀናጀ መልኩ እንደሚያከናውን ጠቁመዋል።
ዘጋቢ: ካሱ ብርሃኑ

More Stories
ህዝበ ክርስቲያኑ የ2019 ዓ.ም የእንቁጣጣሽ በዓልን በሚያከብርበት ወቅት አቅመ ደካሞችን በመደገፍ ሊሆን እንደሚገባ የጠምባሮ ልዩ ወረዳ የሀይማኖት አባቶች ተናገሩ
የ2018 በጀት ዓመት ኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች ታላላቅ ስኬቶችን ያስመዘገበችበት እና የዲጂታል ሽግግር የሉዓላዊነቷ ምሰሶ መሆን የቻለችበት አመት መሆኑን አቶ አልማው ዘውዴ ገለፁ
ጳጕሜን 5 “የነገው ቀን” በኮሬ ዞን በልዩ ልዩ ዝግጅቶች እየተከበረ ነው