‎ዜጎች በነጻነት ድምጻቸውን እንዲሠጡ ፍጹም ሠላማዊ የምርጫ ሂደት ለመፍጠር በቂ ዝግጅት መደረጉ ተገለጸ

‎ዜጎች በነጻነት ድምጻቸውን እንዲሠጡ ፍጹም ሠላማዊ የምርጫ ሂደት ለመፍጠር በቂ ዝግጅት መደረጉ ተገለጸ

‎ሀዋሳ: ግንቦት 22/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) ዜጎች በነጻነት ድምጻቸውን እንዲሠጡ ፍጹም ሠላማዊ የምርጫ ሂደት ለመፍጠር በቂ ዝግጅት መደረጉን የአርባምንጭ ከተማ ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ኮማንደር ክበበው አዳል ገለጹ።

‎7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ፍፁም ሰላማዊ እና ስኬታማ በሆነ መልኩ እንዲጠናቀቅ ከተለያዩ የፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት እየተሠራ መሆኑን ኮማንደሩ ተናግርዋል።

‎በከተማው መጠነ-ሰፊ የሰላም ማስከበር ሥራ እያከናወኑ መሆኑን ጠቁመው፥ ለምርጫው ሂደት ስኬታማነት እጅግ ወሳኝ የሆኑ የምርጫ ቁሳቁሶች በ120 የምርጫ ጣቢያዎች(3 ንዑስ ጣቢያዎችን ጨምሮ) ያለምንም የፀጥታ እንቅፋት እና መስተጓጎል በተፈለገው ቦታ እና ጊዜ በሰላም መሰራጨታቸውን ተናግረዋል።

‎የምርጫው ሂደት ፍፁም ሰላማዊ፣ ነጻ እና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ በሁሉም የከተማው አካባቢዎች የተጀመረው የፀጥታ ጥበቃ እና የክትትል ሥራ ምርጫው ተጠናቅቆ ውጤት እስኪገለጽ ድረስ ይበልጥ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመላክተዋል።

‎በመሆኑም የከተማው ነዋሪዎች እና መራጮች በፍፁም ራስ መተማመን በምርጫው ዕለት በነቂስ ወጥተው ድምፃቸውን እንዲሰጡ ኮማንደር ክበበው ጥሪያቸውን አስተላፈዋል።

‎በየአካባቢው በልዩ ሁኔታ ከተለያዩ የጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት አጠቃላይ የምርጫው ሂደት እስኪጠናቀቅ ድረስ የሰላም እና የሕግ የበላይነትን የማስከበር ኃላፊነታቸው እንደሚወጡ ገልፀዋል።

‎ዘጋቢ: ዘላለም ተስፋዬ