በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ ያሉ ሴቶችን በሙያ ልማት እና በስትራቴጂካዊ አጋርነት የአመራርነት ተሳትፏቸውን ለማሳደግ በትኩረት መስራት እንደሚገባ ተመላከተ

በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ ያሉ ሴቶችን በሙያ ልማት እና በስትራቴጂካዊ አጋርነት የአመራርነት ተሳትፏቸውን ለማሳደግ በትኩረት መስራት እንደሚገባ ተመላከተ

ዩኒቨርሲቲው “Empowering Women in Academic Leadership for Ethiopia” በሚል ርዕስ 3ኛው ሀገር አቀፍ የሴት ምሁራን ወርክሾፕ አካሂዷል።

የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና የቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዝዳት ዶክተር ዮሀንስ ገብሩ፤ ኔትወርኪንግ ሊደርሺፕ በማጠናከር ሴቶች የተሻለ እውቀት እንዲያገኙ እና ልምድ እንዲቀስሙ ለማድረግ መድረኩ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።

በተለይም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ ያሉ ሴቶችን በሙያ ልማት እና በስትራቴጂካዊ አጋርነት የአመራርነት ተሳትፏቸውን ለማሳደግ የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

ለአብነትም ማህበራዊ ጫናዎችን የመቀነስ፣ ዴይኬር የማቋቋም፣ የምርምር የመወዳደሪያ ዘርፍ የማዘጋጀት ተግባር እና ሌሎችም ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል ዶክተር ዮሀንስ።

ሴቶች ጊዜያቸውን በአግባቡ በመጠቀም እራሳቸውን ማብቃትና የተሻለ ደረጃ ማግኘት እንዲችሉ መስራት እንደሚጠበቅባቸውም በመጠቆም።

የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ መምህርትና የአስተዳደር ልማት እና ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር የሺሃረግ አፈራ በበኩላቸው፤ የሴቶች ሃገራዊ ወርክሾፖ እንደ ሃገር ለሶስተኛ ጊዜ የተካሄደ መሆኑን በማንሳት ሴት ምሁራንን እርስ በርስ የማስተሳሰር፣ የማሰልጠንና የማብቃት አንዱ ተግባር እንደሆነም ገልፀዋል።

እንደ ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ሴት አመራሮችን ወደ ፊት በማምጣት እና በማነሳሳት የሴቶች ጫናን ለመቀነስ የሚበረታቱ ተግባራት ቢኖሩም ሴቶች በተፈለገው ልክ የአመራርነት ቦታ ከመያዝ አኳያ ክፍተቶች እንደሚስተዋሉም ዶክተር የሺሃረግ ተናግረዋል።

በቀጣይም ሴቶችን በማብቃት የተገኙ እድሎችን በአግባቡ በመጠቀም ለተሻለ ለውጥ ራሳቸውን ማዘጋጀት ይጠበቅባቸዋልም ብለዋል።

የኢፌዲሪ የትምህርት ሚኒስቴር የመምህራንና የትምህርት አመራር ልማት ባለሙያ ሊድያ ሳንቴ፤ ሴቶችን ወደ አመራርነት ለማምጣት ለበርካታ አመታት ስትራቴጂ ተቀርፆ ሲተገበር መቆየቱን በማስታወስ በተለይም የቤት ውስጥ ጫናን ለመቀነስ የህፃናት መቆያ የማዘጋጀትና አጫጭር ስልጠናዎችን የመስጠት እንዲሁም ሌሎችም ተግባራት መከናወናቸውን አውስተዋል።

የመድረኩ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት ዩኒቨርሲቲው ሴት አመራሮችን ለማብቃት እና ለመደገፍ የሚያደርጋቸው ጥረቶች የሚበረታቱ መሆኑን ገልጸው እንደዚህ አይነት መሰል ወርክሾፖች መዘጋጀታቸው ጠቀሜታው ከፍተኛ መሆኑን አስረድተዋል።

በቀጣይም ሴቶች በራስ የመተማመን አቅማቸውን ለማሳደግ በቁርጠኝነት መስራት ይጠበቃል ብለዋል።

ዘጋቢ፡ እርካብነሽ ወልደማርቆስ – ከወልቂጤ ጣቢያችን