የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ የፍጻሜ ፍልሚያ፡ አርሰናል ከ ፒኤስጂ
ዛሬ ምሽት የዓለም እግር ኳስ አይኖች ሁሉ በሃንጋሪው ፑሽካሽ አሬና ስታዲየም ያርፋሉ።
የዘንድሮው የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ የፍጻሜ ጨዋታ፣ የስልት እና የጥቃት አውድማ ሆኖ የፈረንሳዩን ክለብ ፒኤስጂ እና የእንግሊዙን ክለብ አርሰናል አገናኝቷል።
የአምናው የውድድር ዓመት አሸናፊ የሆነው የፈረንሳዩ ክለብ ፒኤስጂ፣ ዋንጫውን ለማስጠበቅ ወደ ሜዳ ይገባል።
በግማሽ ፍጻሜው የጀርመኑን ባየርን ሙኒክ በመግታት ለፍጻሜ የደረሰው ፒኤስጂ፣ የውድድር ዓመቱ አስፈሪ አጥቂ ቡድን ነው። ክለቡ እስካሁን ባደረጋቸው 16 ጨዋታዎች 44 ግቦችን በማስቆጠር በማጥቃቱ ምን ያህል አደገኛ እንደሆነ አሳይቷል።
ጉዳት ላይ የነበሩት የባሎንዶር አሸናፊው ኦስማን ዴምቤሌ እና አሽራፍ ሀኪሚ ወደ ልምምድ መመለሳቸው ለቡድኑ ትልቅ ጉልበት ሆኗል።
ከእነርሱ በተጨማሪ እንደ ኪቪቻ ክቫረትስኬሊያ፣ ኔቬስ እና ቪቲኒሃ ያሉ ኮከቦች የፒኤስጂን የፊት መስመር እጅግ አስፈሪ አድርገውታል።
በአንጻሩ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ በወርቃማው ዘመኑ ላይ የሚገኘው አርሰናል፣ ከ20 ዓመታት የጥበቃ ጉዞ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በሻምፒዮንስ ሊጉ ለዋንጫው ፍጻሜ ደርሷል።
በአሰልጣኝ ሚኬል አርቴታ የሚመራው “የመድፈኞቹ” ሰራዊት በዘንድሮው የውድድር ዓመት በሻምፒየንስ ሊጉ አንድም ጨዋታ ሳይሸነፍ ለፍጻሜ በመድረሱ፣ ቡድኑን ለመሸነፍ እጅግ ከባድ እንደሆነ አስመስክሯል።
አርሰናል የፒኤስጂን አጥቂዎች ለመግታት የሚያስችል ድንቅ የተከላካይ ክፍል አለው። የግብ ጠባቂው ዴቪድ ራያ ብቃት፣ እንዲሁም የጋብሬል ማጋሌሽ እና ዊሊያም ሳሊባ ጥምረት፣ እስካሁን በውድድር ዓመቱ ተጋጣሚዎች ላይ ያስቆጠሩት 29 ግቦች እና የተቆጠረባቸው 6 ግቦች ብቻ መሆናቸው፣ ቡድኑ በታክቲክ ምን ያህል የተደራጀ እንደሆነ ያሳያል።
ሁለቱ ቡድኖች እርስ በርስ ባደረጓቸው ያለፉት አምስት ጨዋታዎች፣ እያንዳንዳቸው ሁለት ጊዜ ድል ተቀዳጅተው አንድ ጊዜ በአቻ ውጤት ተለያይተዋል። ይህ የሚያሳየው የኃይል ሚዛናቸው እጅግ የተጠጋጋ መሆኑን ነው።
ምሽት 1 ሰዓት ላይ የሚጀምረውን ይህን አጓጊ ጨዋታ ጀርመናዊው ዳኛ ዳንኤል ሴበርት በመሐል ዳኝነት የሚመሩት ይሆናል።
አርሰናል በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ዋንጫውን በማንሳት የአውሮፓ አዲስ ንጉስ ለመሆን ይፋለማል፤ ፒኤስጂ ደግሞ የአውሮፓ የበላይነቱን እንደያዘ ለመቀጠል ይታገላል።
ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ

More Stories
በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ ያሉ ሴቶችን በሙያ ልማት እና በስትራቴጂካዊ አጋርነት የአመራርነት ተሳትፏቸውን ለማሳደግ በትኩረት መስራት እንደሚገባ ተመላከተ
ሀገር ወዳድና በመልካም ስነ-ምግባር የታነፀ ዜጋን ለማፍራት መሠረቱ ቤተሰብ መሆኑ ተገለፀ
የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የድምጽ መስጫ ቀን 2 ቀናት ብቻ ቀርተውታል