ሀገር ወዳድና በመልካም ስነ-ምግባር የታነፀ ዜጋን ለማፍራት መሠረቱ ቤተሰብ መሆኑ ተገለፀ
የሀዲያ ዞን ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ የዓለም አቀፍ የቤተሰብ ቀንን የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በተገኙበት አክብሯል።
የሀዲያ ዞን ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኃላፊ አቶ አዲሴ አውቶ እንደገለጹት፤ መልካም ቤተሰብን መመስረት ሀገር ወዳድና መልካም ትውልድን ለመፍጠር ያለው አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነው።
ለሀገር እድገት አዎንታዊ ሚና የሚጫወት ትውልድ ለመገንባት የሁሉም አካላት ተሳትፎና ርብርብ ወሳኝ መሆኑንም ኃላፊዉ ገልጸዋል።
በቤተሰብ ዉስጥ አንድነትን ማጠናከር ፍቅርን፣ መተሳሰብንና የታማኝነት እሴቶችን እንደሚያጎለብትም አቶ አዲሴ አንስተዋል።
መምሪያውም ይህ ተግባር በሁሉም ህብረተሰብ ዘንድ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አቅዶ እየሠራ መሆኑንም አቶ አዲሴ ገልጸዋል።
ሀገር ወዳድና በመልካም ስነ-ምግባር የታነፀ ዜጋን ለማፍራት መሠረቱ ቤተሰብ መሆኑን አክለዋል።
በዕለቱ የመወያያ ጽሑፍ ያቀረቡት የመምሪያው ባለሙያ አቶ ብርሃኑ ሊሬ በበኩላቸው፤ በልጆች ሁለንተናዊ እድገት ላይ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች የበኩላቸውን ኃላፊነት መወጣት እንዳለባቸው ገልጸዋል።
በልጆች አስተዳደግና ስነ-ልቦና ላይ ተፅዕኖ በሚፈጥሩ እንደ ማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ባሉ ጉዳዮች ዙሪያ ወላጆችና ባለድርሻ አካላት ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር ሊያደርጉ እንደሚገባም በጽሑፋቸው ጠቅሰዋል።
አንዳንድ አስተያየታቸውን የሰጡት የመድረኩ ተሳታፊዎች በበኩላቸው ልጆችን በመልካም ስነ-ምግባር አንጾ በማሳደግ ለሀገር ልማት እንዲበቁ ለማድረግ የቤተሰብ ሚና ከፍተኛ በመሆኑ የድርሻቸውን አንደሚወጡ ተናግረዋል።
በዕለቱም የመልካም ቤተሰብ ተሞክሮ ቀርቦ ውይይት የተደረገ ሲሆን በመድረኩም የሀዲያ ዞን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ ትዕግስት አማኑኤልን ጨምሮ የሀይማኖት ተቋማት፣ የዕድሮች ጥምረት፣ የፍትህ፣ የሴቶችና ህፃናት ቢሮ ተወካዮች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ ሆነዋል።
ዘጋቢ፡ ተሻለ ከበደ – ከሆሳዕና ጣቢያችን

More Stories
የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ የፍጻሜ ፍልሚያ፡ አርሰናል ከ ፒኤስጂ
የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የድምጽ መስጫ ቀን 2 ቀናት ብቻ ቀርተውታል
#South_Radio_And_Television_Agency #ደሬቴድ #ኢትዮጵያ_ትመርጣለች #ምርጫ #ጥሞና #Srta