ተአምረኛው የዘምዘም ውሃ
በመካ የፈለቀው የዘምዘም ዉሃ ታሪካዊ አመጣጥና ስያሜ ከእስማኤል እናት ሀጀራ ጋር የሚገናኝ እንደሆነ የእስልምና እምነት ድርሳናት ያመለክታሉ።
በአረብ በረሃ ዉስጥ ከልጇ እስማኤል ጋር በመሆን በከፋ የዉሃ ጥም የተጎዳችዉ እናት ሀጀራ፥ በሰፍዋና መርዋ መካከል በዉሃ ፍለጋ ላይ ባለችበት ወቅት በድንገት አሸዋን ፈንቅሎ የወጣ ዉሃ አይኗ ላይ ያርፋል።
በወቅቱ ልጇ እስማኤል ወዲያ ማዶ ነበርና እሱን እስክታመጣ ዉሃዉ እንዳያልቅባት ፈርታ ቁም፣ ዝም በል፣ አትፍሰስ አለችው። በአረብኛ ቋንቋ “ዘም፣ዘም” አለችዉ። የዘምዘም ዉሃ ታሪክም ከዚችዉ ዕለት ይጀምራል።
በምድር ዉስጥ የውሃው ጥልቀት 10 ነጥብ 6 ጫማ ከወለል በታች ሲሆን በሰከንድ 8ሺ ሊትር እየመነጨ ሳያቋርጥ ለ24 ሰአታት ወደ ላይ ቢገፋ ከ691 ሚሊየን ሊትር በላይ በቀን ይለቀቃል ማለት ነው። አጃኢብ ነዉ!
የሚገርመው እራሱን መልሶ ለመተካት የሚፈጅበት ጊዜ 11 ደቂቃ ብቻ ነው።
ምንም አይነት ከለርና ሽታ ባይኖረውም የራሱ የሆነ ጣዕም ያለዉ ስለመሆኑ በዘርፉ የተደረጉ ጥናቶች ያመለክታሉ።
የትኛውም ዉሃ የውሃ ጥምን ሊቆርጥ የሚችል ቢሆንም ዘምዘም ዉሃ ግን ረሀብንም ጭምር የሚያስታግስ ስለመሆኑ በዘርፉ የተደረገ ጥናት ያስረዳሉ። በውስጡም ካልሺየም ማግኒዥየም ፍሎራይድና ሌሎችም ንጥረ ነገሮች በመያዙ አንድ ሰው ይሄን ዘምዘም ዉሃ ብቻ እየጠጣ መቆየት ይችላል።
በነዚህ ሁሉ ክፍለ ዘመናት ሲቆይ ጣዕምና ጥራቱ በፍፁም ላለመቀየሩ መነሻ ምክንያት ምን እንደሆነ እስካሁን ሳይንስ ሊደርስበት አልቻለም። በዚህ ዙሪያ እየተደረገ ያለው ጥናትና ምርምር ግን አሁንም እንደቀጠለ ይገኛል።
ከሁሉም በላይ የሚገርመው ይህ ውሃ ሲሞላ እራሱ የሚቆም ሲሆን ከተመደበው በላይ አይመነጭም። በቀን 691 ነጥብ 2 ሚሊየን ሊትር እየመነጨ በአላህ ተአምርና ፍቃድ የሀጀራን ምኞት አስታኮ ለሰዉ ልጆች ጥቅም በመስጠት ላይ ይገኛል።
ተአምረኛው የዘምዘም ዉሃም ፍቱን መድሃኒትና ምግብ ኧረ እንዲያዉም ከውሃም በላይ ሆኖ ቀጥሏል።
የዘምዘም ጉድጓድ እስከዛሬ ድረስ ውሃ እያፈለቀ ይገኛል።
የዘምዘም ውሃ በረከት ያለው ውሃ ነው ተብሎ ስለሚታመን ሐጅና ዑምራ የሚያደርጉ ሙስሊሞች ይጠጣሉ፣ ወደ አገራቸውም ይወስዳሉ።
የሳውዲ አረቢያ መንግሥት ውሃውን በዘመናዊ ስርዓት በማጣራትና በማሰራጨት ለሚሊዮኖች ሐጃጆች እያቀረበ ስለመሆኑ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
አዘጋጅ: መሀመድ ሽሁር – ከወልቂጤ ጣቢያችን

More Stories
ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰኞ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም. የድምፅ መስጫ ቀንን አስመልክቶ የተሰጠ መግለጫ
ዒድ አል አደሀ በዓል በሂጅራ ዘመን አቆጣጠር በዙልሂጃ ወር ዘጠነኛው ቀን ላይ የሚከበር በዓል ነው።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ በተገኙበት በጋሞ ዞን ጨንቻ እና አካባቢው የብልጽግና ፓርቲ የምርጫ ቅስቀሳ ተካሂዷል