የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ በተገኙበት በጋሞ ዞን ጨንቻ እና አካባቢው የብልጽግና ፓርቲ የምርጫ ቅስቀሳ ተካሂዷል
የጨንቻ ከተማ ከንቲባ አቶ ተስፋዬ አገና በመክፈቻ ንግግራቸው እንዳሉት፤ ከተማዋ የዕድሜዋን ያህል ያልለማች ቢሆንም በብልጽግና ዘመን የመብራት፣ የውሃ እና የአስፓልት መንገድ ዝርጋታ ከተማዋን ተጠቃሚ አድርጓታል።
የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን ለማስቀጠል የከተማዋ ሕዝብ የብልጽግና ፓርቲን በመምረጥ አጋርነቱን እንዲያረጋግጥ ጠይቀዋል።
የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ደምሴ አድማሱ (ዶ.ር) ብልጽግና ፓርቲ በዞኑ ብሎም ጨንቻ አካባቢ ተጨባጭ ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊ እና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ አግኝተዋል።
በቀጣይ አምስት ዓመታት ቀሪ የሕዝብ ጥያቄዎችን መመለስ ይችል ዘንድ ሕዝቡ የፓርቲውን የምርጫ ምልክት የሆነውን የስንዴ ነዶ እንዲመርጥ አሳስበዋል።
የብልጽግና ፓርቲ ባለፉት ጊዜያት አገሪቱን መምራት ከጀመረ ወዲህ በአገሪቱ አበረታች የልማት እና የመልካም አስተዳደር ስኬቶች መመዝገባቸው ተገልጿል።
በብልጽግና ምርጫ ቅስቀሳው ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እና የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ አባል አቶ ጥላሁን ከበደ በወረዳው በርካታ የብልጽግና የልማት ትሩፋቶች የተመዘገቡበት እና እየተመዘገቡ ያሉበት ወረዳ መሆኑን አውስተው የወተት፣ የአፕል እና የደጋጎች ምድር የሆነውን የጨንቻን ሕዝብ ይበልጥ ተጠቃሚ ለማድረግ የብልጽግና ፓርቲ እየተጋ ስለመሆኑ ተናግረዋል።
ባለፉት ስምንት ዓመታት የተመዘገቡ ስኬቶች ይበልጥ እንዲጎለብቱ እና ሕዝቡ ኢኮኖሚያዊ ሉአላዊነቱን እንዲያረጋግጥ ህብረተሰቡ ድምጹን ለፓርቲው እንዲሰጥ አቶ ጥላሁን አሳስበዋል።
ጋሞ የሚታወቅበትን የሠላም ዕሴት አጠናክሮ በመያዝ አንድነቱን ይበልጥ እንዲያጎለብት ርዕሰ መስተዳድሩ መክረዋል።
በምርጫ ቅስቀሳው ላይ የጨንቻ ምርጫ ክልል የፌደራል ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዕጩ፣ የክልል ተወካዮች እና የክልልና የጋሞ ዞን አመራሮች እና የጨንቻ ወረዳ እና ቆጎታ ሕዝብ የጨንቻ ከተማ አስተዳደር የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች በምርጫ ቅስቀሳው ላይ ተሣትፈዋል።
ዘጋቢ: ወ/ገብርኤል ላቀው – ከአርባ ምንጭ ጣቢያችን

More Stories
ተአምረኛው የዘምዘም ውሃ
ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰኞ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም. የድምፅ መስጫ ቀንን አስመልክቶ የተሰጠ መግለጫ
ዒድ አል አደሀ በዓል በሂጅራ ዘመን አቆጣጠር በዙልሂጃ ወር ዘጠነኛው ቀን ላይ የሚከበር በዓል ነው።