በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ በየዓመቱ በድምቀት ከሚከበሩ ኃይማኖታዊ በዓላት መካከል የኢድ አል አድሃ በዓል ዋነኛው ነው።

በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ በየዓመቱ በድምቀት ከሚከበሩ ኃይማኖታዊ በዓላት መካከል የኢድ አል አድሃ በዓል ዋነኛው ነው።

አረፋ የሚል ሌላኛው መጠሪያ ያለው ይህ ታላቅ ኃይማኖታዊ በዓል፣ በመላው ዓለም በሚገኙ የእምነቱ ተከታዮች ዘንድ በድምቀት ይከበራል።

የኢድ አል አድሃ አረፋ በዓል በሁሉም የአገሪቱ ክፍል በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ ከፍተኛ ግምት ተሰጥቶት፣ ከኃይማኖታዊ ይዘቱ ባለፈ ባህላዊ እሴቶች ጭምር ተካተውበት በድምቀት እንደሚከበር ይጠቀሳል።

የኢድ አል አድሃ አረፋ በዓል ዘንድሮ ለ1447ኛ ጊዜ የሚከበር ሲሆን፣ በዓሉ ሙሉ በሙሉ በሚባል ሁኔታ ከሐጅ ሥርዓት ጋር የተያያዘ ነው።

የበዓሉ ታሪካዊ ዳራ ሲጠቀስም፣ ኢድ አል አድሃ እንዲሁም የሐጅ ስነ ስርዓት ከነብዩ ኢብራሂም ጋር የተያያዘ ሆኖ ይገኛል።

የበዓሉ ቀን የሚፈጸሙ የእርድ ተግባራትም ይሁኑ ሐጅ የሄዱ ሰዎች አረፋ ተራራ ላይ የሚፈጽሟቸው ሁነቶች በሙሉ ከነቢዩ ኢብራሂም እና ከቤተሰቦቻቸው እንደማይወጡ ይነገራል፡፡

የእምነቱ ተከታዮች ከሚፈጽሟቸው አበይት ተግባራት መካከል የሀጄራን ገድል ለማስታወስ በተራሮች መካከል መመላለስ መሆኑ ይጠቀሳል።

በዓሉ በሚከበርበት ዕለት ህዝበ ሙስሊሙ ወደ ሜዳ በመውጣት የኢድ ሰላት ያከናውናል። ከዚህ መልስም ነው የእርድ ተግባር የሚፈጸመው በዕለቱ ከበዓሉ ጋር በተያያዘ ለሚፈጸምው የእርድ ተግባርም ከግመል፣ በሬ፣ በግ እና ፍየል ውጭ እንዳይሆን ኃይማኖታዊ ትዕዛዝ መኖሩም ነው የሚጠቀሰው።

እርዱ ከተፈጸመ በኋላም አንድ ሶስተኛ የሚሆነው ለቤተሰብ፣ አንድ ሶስተኛው ለጎረቤትና ለዘመድ እንዲሁም አንድ ሶስተኛው ለድሆች የሚሰጥ ሲሆን፣ በዚህ ዕለት ስጋ እጥተው ተርበው የሚውል እንዳይኖሩ በሚል ነው።

ከግመል፣ በሬ፣ በግ እና ፍየል ውጭ ሌላ የእርድ እንስሳት የማይፈጸምበት የተጻፈ ምክንያት ባይኖርም፣ ለምሳሌ የበዓሉ ዕለት ዶሮ ማረድ የማይቻለው ስጋዋን ለማከፋፍል ስለማይበቃ እንደሆነ ይነገራል ።

ለበዓሉ የሚደረገው ዝግጅት በዓሉ ከመድረሱ ቀደም ብለው ባሉት ወራቶች ውስጥ የሚጠናቀቅ ሲሆን፣ እናቶች ለበዓሉ ማድመቂያ የሚሆኑ ቤት እንዳፈራው ያዘጋጃሉ።

ሴቶች ልጆቻቸው ደግሞ የመኖሪያ ቤቶችን በማስዋብ፣ የመመገቢያ ቁሶችን በማጽዳት እና ሌሎች ለበዓሉ የሚያስፈልጉ ቅድመ መሰናዶዎችን በማሟላት ሥራ ተጠምደው ይታያሉ፡፡

እንደ ሴቶቹ ሁሉ ወንዶቹም ቢሆኑ ለአረፋ በዓል የሚያከናውኗቸው የሥራ ድርሻዎች አሏቸው፡፡
ለማገዶ የሚሆን እንጨት ፈልጦ ማዘጋጀት፣ ለእርድ የሚሆን ከብት ማቅረብ የአባቶችና የወንድ ልጆቻቸው ድርሻ ነው።

እንዲሁም የበዓሉ ማህበራዊ ፋይዳ የላቀ መሆኑ የሚነገር ሲሆን፣ በተለይ በከተማ የሚኖሩ የእምነቱ ተከታዮች በገጠር የሚገኙ ዘመዶቻቸውን ለመጠየቅ የሚጠቀሙበት መልካም እድል መሆኑም ይነሳል።

ስለዚህም በሥራ ምክንያት ተራርቆ የቆየውን የሙስሊም ቤተሰብ ከያለበት አሰባስቦ ለማገናኘት የአረፋ በዓል ጥሩ አጋጣሚ ነው፡፡

በተጨማሪም የአረፋ በዓል ቀደም ሲል ተጫጭተው የቆዩ ወጣቶች የሚሞሸሩበት፣ ሌሎችም የወደፊት ትዳራቸውን ለመመስረት የትዳር ጓደኛቸውን የሚመርጡበት እና በባህሉ መሰረት የሚያጩበትም ጭምር መሆኑን የእምነቱ ተከታይ አባቶች ሳይጠቅሱ አያልፉም።

እንዲሁም በተጣሉ ሰዎች መካከል እርቀና ሰላም እንዲወርድ በማስቻል ረገድም የኢድ አል አድሃ አረፋ በዓል ትልቅ ኃይል እንዳለው ነው በእምነቱ አስተምህሮ የሚገለጸው።

ከበዓሉ በፊት የተቀያየሙ ባልና ሚስት፣ ልጅና ወላጆች፣ ጎረቤታሞች እንዲሁም በማህበረሰብ መካከል የተፈጠሩ ያለመግባባቶች ካሉ በአረፋ በዓል ሰሞን ይቅር በመባባል ሰላምን እና እርቅ ያወርዳሉ።

በዚህም በበዓሉ ሰሞን ከመብላት እና መጠጣቱ ባሻገር ሌሎች በርከት ያሉ ቤተሰባዊ እና ማህበራዊ ፋይዳ ያላቸው ተግባራትም ይከናወናሉ።

በታሪኳ በቀለ