ህዝበ ሙስሊሙ የአረፋን በአል ሲያከብር አቅመ ደካሞችና ለተለያዩ ችግር የተጋለጡ ወገኖችን በማገዝ መሆን እንዳለበት በጉራጌ ዞን የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሙራድ ከድር አሳሰቡ

ህዝበ ሙስሊሙ የአረፋን በአል ሲያከብር አቅመ ደካሞችና ለተለያዩ ችግር የተጋለጡ ወገኖችን በማገዝ መሆን እንዳለበት በጉራጌ ዞን የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሙራድ ከድር አሳሰቡ

የከተማው አስተዳደር ከከተማው ባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት ጋር በመተባበር የአረፋ በዓልን ምክንያት በማድረግ ለአረጋውያን ማዕድ አጋርቷል።

የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሙራድ ከድር ማዕድ ባጋሩበት ወቅት እንዳሉት በበአላት ወቅት ማህበረሰቡ ይበልጥ አንድነቱን የሚያጎላበትና የአረፋ በአልን አስታዋሽ ከሌላቸው ወገኖች ጋር አብሮ የማሳለፍ ባህላዊ እሴቱን የሚጠናከርበት በአል ነው።

በዓሉን ከአረጋዊያኑ ጋር ማክበር የተለየ እንደሚያደርገው የገለጹት አቶ ሙራድ፥ በዓሉን ለማክበር ከተለያየ አካባቢ የሚመጡ ታዳሚዎች የአረፋ በዓል ከሀይማኖታዊ ይዘቱ ባለፈ፣ ባህላዊ እሴቱን ለመጠበቅ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን አብራርተዋል።

የመረዳዳትና የመደጋገፍ ባህላዊ እሴቶችን በማጠናከር ለተለያዩ ችግር የተጋለጡ ወገኖች በበዓላት ተደስተዉ እንዲዉሉ ማድረግ ከፍተኛ ፋይዳ ያለው በመሆኑ ይህም ባህላዊ እሴቶቻችን አጠናክረን ማስቀጠል ይገባል ብለዋል።

ህዝበ ሙስሊሙ የአረፋን በአል ሲያከብር እንደተለመደው አቅመ ደካሞችና ለተለያዩ ችግር የተጋለጡ ወገኖችን ማዕድ በማጋራትና በመደገፍ በአብሮነት ማክበር ይኖርበታል ብለዋል።

የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ባህል ቱሪዝም ፅህፈት ቤት ኃላፊ ወ/ሪት ትዕግስት ይርጋ በበኩላቸው በዓላትን ስናስብ አቅመ ደካማ ወገኖችን ታሳቢ በማድረግ መሆን እንዳለበት አስረድተዋል።

በአሉ በፍቅርና በአብሮነት የሚከበር ሲሆን አቅም ለሌላቸዉ ወገኖች የሚሆን አጠቃላይከ 900 ሺ ብር በላይ ወጪ በማድረግ ማዕድ የማጋራት ስራ መሰራቱም ተናግረዋል።

ማህበረሰቡ የመደጋገፍ፣ ተካፍሎ መብላትና የመረዳዳት እሴቱን ያደረገ መሆኑን በመግለጽ ቀጣይ ይህንን አኩሪ ባህል አጠናክሮ ማስቀጠል ይኖርበታል ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የቅዱስ ሚካኤል ካቶሊክ አረጋውያን ማዕከል የስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ደረጀ እስጢፋኖስ በዚሁ ወቅት እንዳሉት በዓላትን ምክንያት በማደረግ በየጊዜው ለማዕከሉ መንግስት እያደረገ ያለው ድጋፍ አመስግነዋል።

ለተቸገሩ ወገኖች ማገዝ በበዓላት ወቅት ብቻ ሳይሆን የየእለት ተግባራችን መሆን አለበት ያሉት አቶ ደረጀ በማዕከሉ ያሉ 150 አረጋውያን ቀጣይ ሁሉንም እገዛ እንዲያደርግ ሲሉም ጠይቀዋል ።

በእለቱም ማዕድ የተጋራላቸው የማህበረሰብ ክፍሎች በሰጡት አስተያየትም ለተደረጋለቸዉ ማዕድ ማጋራት በደስታና በፍቅር እንድናሳልፍ አድርጎናል ሲሉ ገልፀዋል።

ዘጋቢ፡ ዝናሽ ሙሉጌታ – ከወልቂጤ ጣቢያችን