አረፋ የእዝነትና የመታዘዝ በዓል በመሆኑ ህዝበ ሙስሊሙ የመተባበርና የመከባበር ዕሴቱን ሊያጠናክር እንደሚገባ ተገለጸ
ሀዋሳ፡ ግንቦት 19/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) አረፋ የእዝነትና የመታዘዝ በዓል በመሆኑ ህዝበ ሙስሊሙ የመተባበርና የመከባበር ዕሴቱን በማጠናከር በዓሉን ሊያከብር እንደሚገባ የሀዲያ ዞን እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ዋና ሰብሳቢ ኡስታዝ ሱልጣን ኡስማን አሳሰቡ።
ለ1ሺ 447 ጊዜ የሚከበረው የኢድ አል አደሃ (አረፋ) በዓል በማስመልከት የእንኳን አደረሳችሁ የመልካም ምኞት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
የሀድያ ዞን እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ዋና ሰብሳቢ ኡስታዝ ሱልጣን ኡስማን የአረፋ በዓልን በማስመልከት ከጣቢያችን ጋር ባደረጉት ቆይታ አረፋ በሀዲሶች ሰፍሮ እንደሚገኘው አደምና ሃዋ በጄነት ላይ ሲኖሩ ፈጣሪ አትብሉ ያለውን የዛፍ ፍሬ በመብለት ሁሉቱም ወደተለያዩ አከባቢዎች ከሄዱ በኃላ የተገናኙት ስፍራ የአረፋ ሜዳ እንደሚባል ገልፀዋል።
ኡስታዝ ሱልጣን አክለውም ፈጣሪ ለነቢዩ ኢብራሂም ልጁን እስማኤልን እንዲሰዋ በጠየቀው ጊዜ ኢብራሂም የፈጣሪን ትዕዛዝ በመቀበል ልጃቸውን ለመሰዋት ሲያዘጋጁ ፈጣሪ በምትኩ የበግ ሙክት ያቀረበበት ታዛዥነታቸውንም የተመለከተበት ድንቅ በዓል መሆኑን አመላክተዋል።
የእምነቱ ተከታዮችም ፈጣሪ ለሰው ልጆች ርሁሩና አዛኝ መሆኑን ያሳየበት በመሆኑ ህዝበ ሙስሊሙ እርስ በእርስ መከባበርና መታዘዝ እንደሚገባ ኡስታዝ ሱልጣን አፆኖት ሰጥተዋል።
በበዓሉ ትልቅ ስፍራ የሚሰጠው የኡዱሁያ ስርዓት ተጠቃሽ መሆኑን ያወሱት ኡስታዙ፥ ለበዓሉ የሚታረዳው አንድ ሶስተኛውን ለነዲያን እና ለምስኪኖች እንዲሰጥ ሀይማኖቱ በጥብቅ ያዛል ብለዋል።
በዓሉ ከሩቅም ከቅርብም ያሉ የሚገናኙበትና የሚዘያየሩበት እንደመሆኑ ለማህበራዊ ዕሴት መጎልበት ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው የምክር ቤቱ ሰብሳቢ ጠቁመዋል።
የዘንድሮውን የአረፋ በዓል ሀገራችን 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ ከምታከሄድበት ወቅት ላይ መከበሩ ልዩ ያደርገዋል ያሉት ኡስታዝ ሱልጣን፥ ሙስሊሙ ማህበረሰብ የአከባቢውን ሰላም በመጠበቅ እና በምርጫው በንቃት በመሳተፍ የበኩሉን ኃላፊነት መውጣት እንደሚገባ አፅኖት ሰጥተዋል።
በመጨረሻም በዓሉ የሰላምና የአንድነት የፍቅር እንዲሆን በመመኘት ለመላው የእምነቱ ተከታዮች የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ዘጋቢ: ሄኖስ ካሳ – ከሆሳዕና ጣቢያችን

More Stories
በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ በየዓመቱ በድምቀት ከሚከበሩ ኃይማኖታዊ በዓላት መካከል የኢድ አል አድሃ በዓል ዋነኛው ነው።
ህዝበ ሙስሊሙ የአረፋን በአል ሲያከብር አቅመ ደካሞችና ለተለያዩ ችግር የተጋለጡ ወገኖችን በማገዝ መሆን እንዳለበት በጉራጌ ዞን የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሙራድ ከድር አሳሰቡ
የአረፋ በዓል ባህላዊ ስርዓትና አከበበር በስልጤ