የአረፋ በዓል ባህላዊ ስርዓትና አከበበር በስልጤ

የአረፋ በዓል ባህላዊ ስርዓትና አከበበር በስልጤ

የኢድ አል -አድሃ የአረፋ በዓል ከእስልምና ሀይማኖት አምስቱ መሰረቶች ውስጥ አንዱ ከሆነው ከሀጅ ስነ-ስርዓት (የአላህን አቤት ከዕባን ከመዘየር) ጋር የተያያዘ ሲሆን፥ የበዓሉ ስም በእስልማና ታሪክ ትልቅ ቦታ ካለው ከአረፋ ተራራ ጋር የተሳሰረ ነው፡፡ የአረፋ ተራራ በሳዑዲ አረቢያ መካ ከተማ አካባቢ ከሚገኙት ተራሮች አንዱ ሲሆን አደምና ሃዋ (አደም እና ሄዋን) አሏህ እንዳይበሉት ከልክሎአቸው የነበረው ዘር በመብላታቸው የተነሳ ተቆጥቶባቸው ከነበሩበት የጀነት ዓለም(ገነት) አስወጥቶ ወደ ምድር ካመጣቸው በኋላ ለብዙ ዘመናት እንዳይገናኙ በማድረግ አራርቆ ካኖራቸው በኋላ ታርቋቸው እንዲገናኙ በመፍቀዱ የተገናኙበት ስፍራ (ተራራ) እንደሆነ ይገለጻል ፡፡

በኢድ-አል አድሃ አረፋ ከሚከናወኑት ሀይማኖታዊ ተግባራት ውስጥ የሐጅ ስርዓት ማከናወን፣ (ከዕባን) መጠወፍ (መዞር )እንዲሁም ኡዱህያ(ዕርድ) ማከናወን ዋነኞቹ ናቸው፡፡

በሀገራችን ኢትዮጵያ ውስጥ የኢድ-አል አድሃ የአረፋ በዓል በደማቁ ከሚያከብሩ አካባቢዎች መከከል የስልጤ ማህበረሰብ አንዱ ነው፡፡ በከተማ የሚኖረው የአከባቢው ተወላጅ (ፋኞ) ለበዓሉ ወደ አካባቢው የሚተምበት፣ የናፈቁትን ወላጅ፣ ጎረቤት ፣ዘመዶቹን የተለያዩ ስጦታዎችን በመያዝ የሚጠይቅበት ፤ ወላጆች ልጆቻቸውን (የባቦ) ይምጣልኝ ብለው ሲቀበሉ ልጃገረዶች ደግሞ በተለያዩ ባህላዊ ዜማዎች በማዜም እንግዶችን ይቀበላሉ ።

እዬ እዬ ያባቢዎ
እዬ እዬ ያባቢዎ
አባቤ በሉሼ አበዜ ነዱሼ፣በቁኜም ቤላሼ
እዬ እዬ ያባቢዎ
እዬ እዬ ያባቢዎ
የአረፋይ ከራባ አዋጣይ ወራባ
እዬ እዬ ያባቢዎ
እዬ እዬ ያባቢዎ
በዜጋይ አንገዶ እጎሬን ዘገዶ
በዱሬሻ አንገዶ እትኩላላን ቡርዶ
እዬ እዬ ያባቢዎ
እዬ እዬ ያባቢዎ
ያባቢዎ እዬ እዬ ያባቢዎ….

በስልጤ ብሔረሰብ አረፋ ከመድረሱ ቀደም ብሎ በእያንዳንዱ ቤተሰብ ከፍተኛ ዝግጅት ይጀመራል፡፡ የቤተሰብ አባላት ልጃገረዶች ፣ወጣቶች፣ ወላጆች የስራ ድርሻ በመውሰድ ለበዓሉ ማድመቂያ የተለያዩ የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን ያከናውናሉ።

እናቶች (ሴቶች) ቅቤና አይብ “ኡጆ” በሚባል በህላዊ ስርዓት የሚሰበስቡ ሲሆን ለአረፋ ተብሎ የተዘጋጀውን እንሰት በመፋቅ ቆጮ፣ ቡላና ቅመማ ቅመም እንዲሁም የተለያዩ ባህላዊ ቁሳቁስችን (ብጥር፣ ቀርሼ፣መከተፌና ጎሎዶ…)የተሰኙትን ከወራቶች ቀደም ብለው ያዘጋጃሉ፣ ይሸምታሉ።

ወንዶች (አባቶች) ለአረፋ በዓል የሚያከናውኗቸው የስራ ድርሻዎች አሏቸው፡፡ ለአረፋ እርድ (ኡድህያ) የሚሆን የሰባ ከብት ከሁለት እስከ ሰባት የሚደርሱ አባወራዎች በጋራ በመሆን ቅርጨ (ማንገዝ) ያዘጋጃሉ ።

ወጣት ወንዶች (ሃርዴ፣ አልቡላ) በዓሉ ወራቶች ሲቀሩት ጀምሮ ለማገዶ የሚሆን እንጨት ፈልጦ ማዘጋጀትና ማቅረብ እንዲሁም አጥር በማጠር አከባቢ ማሳመር ፣በሀገሪቱ በተለያዩ ከተሞች የሚኖሩ የብሔረሰቡ ተወላጆች(ፋኞ) መቀበል በወጣት ወንድ ልጆች አማካይነት የሚከወን ይሆናል፡፡

ልጃገረዶች (ገረጃ፣ አፍቶ) መኖሪያ ቤቶችን (ጋር-ዘገር) በተለያዩ የማስዋቢያ ቀለማት ማለትም የብሔረሰቡ መገለጫ በሆኑት (ነዞ፣በርበሮ፣ቦርጀ፣) በመጠቀም ይቀባሉ፣ ልብስ ያጥባሉ፣ግቢን ያፀዳሉ፡፡

በበዓሉ ወዜማ በተለያዩ አካባቢዎች የሚኖሩ የብሔረሰቡ ተወላጆች ለወላጆቻቸው ስጦታ በመያዝ ወደ የአካባቢያቸው ይገባሉ፡፡ በአረፋ ወደ ቤተሰቡ ያልመጣ በሕይወት እንደሌለ ይቆጠራል፤ የሚቀርበትን ምክንያት ቀድሞ ካላሳወቀ በስተቀር ፣ ቤተሰብንም ሥጋት ላይ ይጥላል፡፡

ሌላኛው በበዓሉ ዋዜማ (ዙል ሒጃ 9) የሚከበረው የሴቶች አረፋ (ዪንዳች አረፋ) ሲሆን ሴቶች (እናቶች) ክልፋን ፣ፍንታፍንቶ (የተከተፈ ጐመን) አተካና ቡላ፣ አይብ፣ቅቤና እንዲሁም የተለያዩ ባህላዊ ምግቦችን በመዘርጋት ቤተሰቦቻቸውን፣ጎሮቤት ፣ወዳጅ-ዘመዶቻቸውን ይመግባሉ ፤ይጋብዛሉ ፡፡

ወንዶች (አባቶች) ደግሞ የበዓሉ ስግደት(ዒድ )በሚከናወንበት ዕለት (ዙል ሒጃ 10 ) ቀደም ብሎ ለአረፋ የተዘጋጀው ሰንጋ በሽማግሌዎች ከተመረቀ (ጀባ) ከተባለ በኋላ በታላቅ የቅርጫው አባላት ቤት እርድ (ኡድህያ) በማከናወን ስጋውን ያከፋፍላሉ ።ከቅርጫው ስጋ አንድ ምድብ በማንሳት ለድሆች የሚያከፋፍሉ ሲሆን ከስጋው ሹሉዳ (ሹሉደ) የሚባለውን ክፍል ለይተው በማውጣት በአከባቢው ለምትገኝ አራስ ወይም በጊዜው ለተገረዙ ወንድ ልጆች ያከፋፍላሉ፡፡ የቤቱ አባወራ(አባት) በበዓሉ ማግስት ጠዋት ደግሞ ከስጋው ከትፎ በማዘጋጀት ቁርስ (ግንዝር) ቤተሰቦቻቸውን ያበላሉ፤ ያጠጣሉ።

በበዓሉ ዕለት እርድ ተከናውኖ ቅርጫው ሲከፋፈል ከስጋው ሸኛው የሚቀመጥ ሲሆን የአረፋ በዓል በተከበረ በአራተኛው ቀን ደግሞ በታላቅ የቅርጫው አባላት ቤት ሻኛ (ፎላ) በጋራ ተሰብስቦ የመብላት ስነ ስርዓት ይከናወናል።

“አንገብሶ ተፎለ ለፈቄ ጄሬነ”
ሊበሉይ ፈሬነ ፣ገረድ ተገራዲ ሊመጡ ቄሬነ”

የአረፋ በዓል በስልጤ ብሔረሰቡ ዘንድ ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጠውና ዝግጅት የሚደርግበት የተለያዩ የቤተሰብ አባላት የሚገናኙበት ስጦታ የሚለዋወጡበት በአብዛኛው የመተጫጫ የጋብቻ ወቅት ነው፡፡የአረፋ በዓል ቀደም ሲል ተጫጭተው የቆዩ የሚሞሸሩበት፣ ሌሎች ትዳር ለመመስረት የትዳር ጓደኛቸውን የሚመርጡበትና በባህሉ መሰረት የሚያጩበትም ጭምር ነው፡፡

የአረፋ በዓልን በስልጤ ልዩ ድምቀት የሚሰጠው ሌላኛው ኩነት ሙዚቃ (ሽባል) ሲሆን ከጥንት ጀምሮ የአረፋ በዓልን ባህላዊ ትውፊት የሚያንጸባርቁ ፣የበዓሉን መድረስ የሚያበስሩ የተለያዩ የሙዚቃ ስራዎች ከወጣት እስከ አንጋፋ ባሉ የብሔረሰቡ በርካታ ድምፃዊያን የተዜሙ የሙዚቃ የጥበብ ስራዎቻቸው አረፋን ያደምቃሉ።

ደች አረፋ መጫን በይዶን
አቦት-እንደት እዘይርቡያን
ደች አረፋ መጫን ባይዶን ባደነ እገብናና በፍራን
**
ፍቼይ አረፋይ ጄጃና፤ ፍቼይ አረፋይ መጣና
ባዴ ሰቤ ቀልቤ ኤከሳና
ያባቢዎ ሴ ያባቢዎ
ያባቢዎ ሴ ያባቢዎ
**
ቴከሰኝ ባዴያ ለሂድ ለዝያራ
አረፋይ ጄጃና ያፍራኒ ማሸረ
ያባባቤ ያባቤዎ…

ከላይ የተገለፁት ሁሉም ባህላዊ የአረፋ የሙዚቃ ስራዎች አረፋ ለመሄድ ልቤ ተነስተዋል፣ ቤተሰብ ወዳጆቼን ለማየት ጓግቼያለሁ፣አረፋ ተራርቀው የቆዩ ቤተሰቦች የሚገናኙበት መሆኑን ፣የአረፋ ትዝታዎችንና ናፍቆትን የሚገልፁ ናቸው ።

ሌላው አረፋ በስልጤ ዘርፈ-ብዙ ማህበራዊ ፋይዳ ያለው በመሆኑ ከበዓሉ በፊት የተቀያየሙ ባልና ሚስት፣ልጅና ወላጅ፣ ጎረቤታሞች ያሉ አለመግባባቶች በአረፋ ሰሞን ይቅር “አውፋቱሊላህ) ተባብለው ሰላምን ያወርዳሉ፡፡ ይህ ከተከናወነ በኃላ ለበዓሉ የተዘጋጀውን ምግብና መጠጥ አብረው በመብላትና በመጠጣት ይደሰታሉ፡፡

ለአረፋ ወደ ቤተሰቦቻቸው የተመለሱ ወጣቶች በቀጣይ የቤተሰብ ህይወት እንዲሻሻል ምንመደረግ አለበት? የሃገሪቷ ሰላም እንዲሰፍንና በአካባቢው ልማት እንዲስፋፋ በአንድነት ከቤተሰብ እና ከማህበረሰቡ ጋር ይመክራሉ፣ የተለያዩ የልማት ስራዎችን በማከናወን ፣ቤተሰቦቻቸውና በአከባቢው ተመርቀው (ለይዶይ የውርዳን የጂጅና) በማለት ወደ የመጡበት በፍቅርና በስስት ይሸኛሉ ።

በአጠቃላይ የኢድ-አል አድሃ የአረፋ በዓል በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ ከፍተኛ ግምት ተሰጥቶት የሚከበር በዓል ሲሆን ከመብላትና መጠጣቱ ባሻገር ሌሎች በርከት ያሉ ቤተሰባዊና ማህበራዊ ፋይዳዎች ጭምር ያሉት እንደሆነ ይታወቃል፡፡

አዘጋጅ: ሙጂብ ጁሀር – ከሆሳዕና ጣቢያችን