ለዒድ አል-አድሃ (አረፋ) በዓል የሚፈጸሙ የቁም እንስሳት እርድ ህብረተሰቡ በቄራ እንዲፈጽም እና ለተረፈ ምርት አወጋገድ ከፍተኛ ትኩረት እንዲሰጥ ጥሪ ቀረበ

ለዒድ አል-አድሃ (አረፋ) በዓል የሚፈጸሙ የቁም እንስሳት እርድ ህብረተሰቡ በቄራ እንዲፈጽም እና ለተረፈ ምርት አወጋገድ ከፍተኛ ትኩረት እንዲሰጥ ጥሪ ቀረበ

የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎቶች ጽህፈት ቤት በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ ለሚከበረው ለ1ሺ 447ኛው የዒድ አል-አድሃ (አረፋ) በዓል የሚፈጸሙ የቁም እንስሳት እርድ፥ ህብረተሰቡ በቄራ እንዲፈጽም እና ለተረፈ ምርት አወጋገድ ከፍተኛ ትኩረት እንዲሰጥ ጥሪ ቀርቧል።

የሆሳዕና ከተማ ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ጽህፈት ቤት ምክትል ሥራ አስኪያጅ እና የመሰረተ ልማት ዘርፍ ኃላፊ አቶ አብነት አባቢያ ​እንደገለጹት መንግስት በአሁኑ ወቅት ለከተሞች ውበት፣ ጽዳትና ለኮሪደር ልማት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ በስፋት እየሰራ ነው።

በበዓል ወቅት ከእንሰሳት እርድ የሚወጡ ተረፈ ምርቶችንና ቆሻሻዎችን ያለምንም ጥንቃቄ በየመንገዱ፣ በኮሪደር ልማት በተሰሩ ውብ የእግር መረማመጃዎችና በየቦዮች ከመጣል ሁሉም ህብረተሰብ መቆጠብ እንደለበት አሳስበዋል።

​በበዓል ወቅት የሚስተዋሉና የከተማዋን ገጽታ የሚያበላሹ ልማዳዊ አሰራሮችን ለማስቀረት ህብረተሰቡ በበዓሉ ወቅት የሚያከናውነውን ማንኛውንም የቁም እንስሳት እርድ በቄራ እንድፈጽሙ ጠቁመዋል።

ህብረተሰቡ ቆሻሻዎችን በተገቢ በመሰብሰብ ለዚሁ ተግባር በተሰማሩ አከላት ላይ መድረስ እንዳላባቸው ጠቁመዋል።

​የሆሳዕና ከተማን ጽዳትና ውበት መጠበቅ የማዘጋጃ ቤቱ ብቻ ሳይሆን የሁሉም ነዋሪ የጋራ ሃላፊነት መሆኑን የጠቁመት ምክትል ስራ አስኪያጁ ፤ ህብረተሰቡ የአካባቢውን ጽዳት በመጠበቅና ይሄንን መመሪያ በተግባር በመተርጎም በዓሉን በታላቅ የኃላፊነት ስሜት እንዲያከብር ጥሪውን አስተላልፏል።

​በመጨረሻም አቶ አብነት መላው የእስልምና እምነት ተከታዮች ለ1ሺ 447ኛው የዒድ አል-አድሃ (አረፋ) በዓል በሰላም አደረሳችሁ የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል ።

ዘጋቢ: ታምራት አለሙ – ከሆሳዕና ጣቢያችን