የተቀናጀ የመረጃ አስተዳደርና ኮሙዩኒኬሽን ስርዓት በመፍጠር ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ በትኩረት ሊሠራ እንደሚገባ ተገለጸ
ሀዋሳ፡ ግንቦት 18/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) የተቀናጀ የመረጃ አስተዳደርና ኮሙዩኒኬሽን ስርዓት በመፍጠር ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ በትኩረት ሊሠራ እንደሚገባ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፍቅሬ አማን ገለጹ፡፡
በክልሉ በየደረጃው ለሚገኙ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች “ዘመናዊ የመረጃ አያያዝ ለላቀ ተቋማዊ ስኬት” በሚል መሪ ቃል የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና በቦንጋ ከተማ ተካሂዷል።
በክልሉ ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ በቴክኖሎጂ የተደገፈ ከእጅ ንክኪ ነጻ የሆነ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ተግባር እየተከናወነ እንደሚገኝ የገለጹት የክልሉ የመንግሥት ዋና ተጠሪ አቶ ፍቅሬ አማን ለሥልጠናው ተሳታፊዎች ባስተላለፉት መልዕክት፥ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት የቴክኖሎጂ አገልግሎት አሰጣጡን ተደራሽ በማድረግ ለዜጎች ሁለተናዊ ተጠቃሚነት እንደሚሠሩ ገልጸዋል።
እንደአገር የተጀመረውን ዲጂታል ኢትዮጵያ እውን ለማድረግ በአሠራር፣ በመረጃ አያያዝና በአገልግሎት አሰጣጥ ዘርፍ የሚታየውን ክፍተት ለመሸፈን እየተሠራ መሆኑም አስረድተዋል።
የአገልግሎት አሰጣጥ ዘርፉን በማዘመን ለተጠቃሚዎች ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር እስከታችኛው መዋቅር በትኩረትና በትብብር እንደሚሠራ አብራርተዋል።
በቀጣይ ለሚከናወኑ ተግባራት ውጤታማነትና ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ላይ ትኩረት ተደርጎ ሊሠራ እንደሚገባ የገለጹት ደግሞ በዕለቱ የተገኙ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ ናቸው።
በሥልጠናው የተገኙ በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች ገንቢ አስተያየት ሰጥተዋል።
ለዚህ ዓይነት ኢንቬቲቭ ስኬት የአመራሩ ቁርጠኝነት ወሣኝና አይተኬ ሚና መኖሩ ተገልጿል።
የክልሉ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ለመረጃ አያያዝ ተግባራዊነት የሚያገለግል ሶፍት ዌር አበልጽጎ አስመርቋል።
ለተግባሩ ስኬት የበኩላቸውን ድርሻ ላበረከቱ ግለሰቦችና ለባሮ ቴክ ዕውቅና ሰርተፊኬት ተሰጥቷል።
በሥልጠናው የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ አቶ ወንድሙ ኩርታን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች፣ ከዞኖችና ከየወረዳዎች የተወጣጡ አመራሮች የሥልጠናው ተሳታፊ ሆነዋል።
ዘጋቢ፡ መሣይ መሠለ – ከቦንጋ ማስተባበሪያ

More Stories
ህዝበ ክርስቲያኑ የ2019 ዓ.ም የእንቁጣጣሽ በዓልን በሚያከብርበት ወቅት አቅመ ደካሞችን በመደገፍ ሊሆን እንደሚገባ የጠምባሮ ልዩ ወረዳ የሀይማኖት አባቶች ተናገሩ
የ2018 በጀት ዓመት ኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች ታላላቅ ስኬቶችን ያስመዘገበችበት እና የዲጂታል ሽግግር የሉዓላዊነቷ ምሰሶ መሆን የቻለችበት አመት መሆኑን አቶ አልማው ዘውዴ ገለፁ
ጳጕሜን 5 “የነገው ቀን” በኮሬ ዞን በልዩ ልዩ ዝግጅቶች እየተከበረ ነው