የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) 1 ሺ 447ኛው የዒድ አል-አድሃ (ዓረፋ) በዓልን በማስመልከት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ
የመልዕክቱ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡
ለመላው የእስልምና እምነት ተከታዮች እንኳን ለ1 ሺ 447ኛው የዒድ አል-አድሃ (ዓረፋ) በዓል በሠላም አደረሳችሁ! እያልኩ መልካም ምኞቴን እገልፃለሁ።
ዒድ አል-አድሃ ሙባረክ!
በሕዝበ ሙስሊሙ ዘንድ በልዩ ልዩ ሃይማኖታዊ ስነ-ስርዓቶች በድምቀት ከሚከበሩት በዓላት መካከል አንዱ የሆነዉ፣ የዒድ አል-አድሃ (ዓረፋ) በዓል ከሃይማኖታዊ አስተምህሮቶቹ ባሻገር ማህበራዊ መስተጋብሮች እንዲነቃቁ፣ የመረዳዳትና የመደጋገፍ እሴቶችና ትዉፊቶች እንዲጠናከሩ መልካም አጋጣሚ ይፈጥራል፤ ተካፍሎ የመብላትን፣ ለተቸገሩ የመድረስን፣ የሌሎችን ችግር ለማቃለል የመነሳሳት ሥነ ልቦናን ከፍ ያደርጋል።
በተለያዩ የሀገራችን ከተሞች፣ በተለያዩ የሕይወት መስኮች ተሰማርተው የሚገኙ የክልላችን ተወላጆች፣ ወላጆቻቸውን፣ ቤተዘመዶቻቸውን የሚጠይቁበት፣ የሐሴትና የፍቅር መንፈስ የሚጎላበት፣ ልጆች በወላጆቻቸው ምርቃት በረከትን የሚላበሱበት፣ ተስፋቸውም የሚለመልምበት ነው – የዓረፋ በዓል።
ይህን የአብሮነትና የመደጋገፍ እሴት ሕዝበ ሙስሊሙ አጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል።
የዘንድሮው የዒድ አል-አድሃ (ዓረፋ) በዓል እየተከበረ የሚገኘው፣ ሀገራችን – ኢትዮጵያ ሰባተኛውን ጠቅላላ ምርጫ እያከናወነች በምትገኝበት እና ለድምፅ መስጫው ዕለትም በጣት የሚቆጠሩ ቀናት በቀሩበት ዋዜማ ላይ ነው።
ስለሆነም መላው ሕዝበ ሙስሊም እና መላው የክልላችን ሕዝቦች ምርጫው ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የበኩላችሁን ከመወጣት ባሻገር በድምፅ መስጫው ዕለት ማልዳችሁ ድምፅ ለመስጠት ከወዲሁ እንድትዘጋጁ ጥሪ አቀርባለሁ !
መልካም የዒድ አል-አድሃ (ዓረፋ) በዓል!
አመሠግናለሁ !

More Stories
የተቀናጀ የመረጃ አስተዳደርና ኮሙዩኒኬሽን ስርዓት በመፍጠር ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ በትኩረት ሊሠራ እንደሚገባ ተገለጸ
የ1ሺ 447ኛው የአረፋ በዓል በሰላም እንዲጠናቀቅ ሰፊ ቅድመ ዝግጅት ሥራዎች መከናወናቸውን ተገለጸ
የብልጽግና ፓርቲ በርካታ ችግሮችን አስወግዶ የሚጨበጥ ተስፋና ነገን በብቃት ለመተለም የሚያስችል ራዕይ ሰንቆ እየሰራ እንዳለ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አበባየሁ ታደሰ (ዶ/ር) ገለጹ