የ1ሺ 447ኛው የአረፋ በዓል በሰላም እንዲጠናቀቅ ሰፊ ቅድመ ዝግጅት ሥራዎች መከናወናቸውን ተገለጸ
ሀዋሳ፡ ግንቦት 18/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የ1ሺ 447ኛው የአረፋ በዓል በሰላም እንዲጠናቀቅ ሰፊ ቅድመ ዝግጅት ሥራዎች መከናወናቸውን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ገለፀ።
በመላው የእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ በታላቅ ድምቀት የሚከበረው የ1ሺ 447ኛው የዒድ አል-አድሃ አረፋ በዓል በክልሉ በሚገኙ ሁሉም አካባቢዎች በሰላማዊ መንገድ ተከብሮ እንዲጠናቀቅ የሚያስችሉ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች መጠናቀቃቸውን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነርና የወንጀልና ትራፊክ አደጋ መከላከል ዘርፍ ኃላፊ አብርሃም ቲርካሶ እንደገለፁት፥ በዓሉ የሰላምና የደስታ እንዲሆን ለማድረግ የጸጥታ መዋቅሩ ከሕዝቡ ጋር በቅንጅት እየሠራ ነው።
በዓሉ ያለ ምንም የጸጥታ ችግር በታቀደው መሠረት በሰላም እንዲጠናቀቅ በየደረጃው በሚገኙ የክልሉ መዋቅሮች፣ ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች በሙሉ ስምሪት ተሰጥቶ ሰፊ ዝግጅት መደረጉን ምክትል ኮሚሽነሩ አረጋግጠዋል።
ምክትል ኮሚሽነር አብርሃም አክለውም የቅድመ ዝግጅት ሥራው በዋናነት ትኩረት ያደረገው የጸጥታ ኃይሉንና የሕዝቡን አጋርነት በማጠናከር ላይ ነው ብለዋል።
የክልሉ ፖሊስ፣ ከሌሎች ባለድርሻ አካለት ጋር በመቀናጀት በየአካባቢው ጥብቅ የክትትልና የጥበቃ ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
ከበዓሉ ቀደም ብሎ ከሃይማኖት አባቶችና ከተለያዩ ኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር ውይይቶች የተደረጉ ሲሆን፥ ኅብረተሰቡ ለአካባቢው ሰላምና መረጋጋት የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች ተሰርተዋል ብለዋል።
በዓሉ በሚከበርባቸው መስጊዶችና የሕዝብ መሰብሰቢያ አደባባዮች ላይ ሕዝበ ሙስሊሙ ያለምንም ስጋት ሶላቱንና ሃይማኖታዊ ሥነ-ሥርዓቱን ማከናወን እንዲችል ልዩ የጥበቃ ስምሪት መዘጋጀቱ ተናግረዋል።
ከዚህ በተጨማሪም በዓልን ለማክበር የእምነቱ ተከታዮች ከተለያዩ ሀገርቱ አከባቢዎች ወደ ክልሉ እየመጡ ስለሆነ የሰዎችንና የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ፍሰት ከግምት ውስጥ በማስገባት፥ ከክልሉ መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ ጋር በጋራ በመሆን የትራፊክ አደጋ እንዳይከሰትና የትራንስፖርት መስተጓጎል እንዳይኖር ስምሪት መሰጠቱን ገልጸዋል።
ህብረተሰቡ ማንኛውንም አጠራጣሪ እንቅስቃሴ ወይም የጸጥታ ስጋት ሲመለከት በአቅራቢያው ለሚገኝ የጸጥታ አካል ፈጣን ጥቆማ በመስጠት፣ ከፖሊስ ጎን ሆኖ የበዓሉን ሰላማዊነት እንዲያረጋግጥ ጥሪ አቅርበዋል።
ምክትል ኮሚሽነሩ በመጨረሻም፥ ለመላው የእስልምና እምነት ተከታዮች ለ1ሺ 447ኛው የዒድ አል-አድሃ (አረፋ) በዓል በሰላም አደረሳችሁ በማለት መልካም ምኞታቸውን አስተላልፈዋል ።
ዘጋቢ: ታምራት አለሙ – ከሆሳዕና ጣቢያችን

More Stories
የተቀናጀ የመረጃ አስተዳደርና ኮሙዩኒኬሽን ስርዓት በመፍጠር ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ በትኩረት ሊሠራ እንደሚገባ ተገለጸ
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) 1 ሺ 447ኛው የዒድ አል-አድሃ (ዓረፋ) በዓልን በማስመልከት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ
የብልጽግና ፓርቲ በርካታ ችግሮችን አስወግዶ የሚጨበጥ ተስፋና ነገን በብቃት ለመተለም የሚያስችል ራዕይ ሰንቆ እየሰራ እንዳለ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አበባየሁ ታደሰ (ዶ/ር) ገለጹ