‎የብልጽግና ፓርቲ በርካታ ችግሮችን አስወግዶ የሚጨበጥ ተስፋና ነገን በብቃት ለመተለም የሚያስችል ራዕይ ሰንቆ እየሰራ እንዳለ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አበባየሁ ታደሰ (ዶ/ር) ገለጹ

‎የብልጽግና ፓርቲ በርካታ ችግሮችን አስወግዶ የሚጨበጥ ተስፋና ነገን በብቃት ለመተለም የሚያስችል ራዕይ ሰንቆ እየሰራ እንዳለ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አበባየሁ ታደሰ (ዶ/ር) ገለጹ

‎የብልጽግና ፓርቲ ዞናዊ የማጠቃለያ የምርጫ ቅስቀሳውን በጌዴኦ ዞን ዲላ ከተማ አካሂዷል።

‎የዲላ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ መስፍን ደምሴ (ዶ/ር) የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ባደረጉበት ወቅት፤ ብልጽግና ፓርቲ ሀገር ሲረከብ የነበሩ በርካታ ችግሮችን በማስተካከል ዛሬ ላይ በርካታ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ስኬቶች ተመዝግበዋል ብለዋል።

‎የዲላ ከተማ ወደ ሪጂዮ ፖሊስ ከተማ ያደገችበት ነው ያሉት መስፍን ደምሴ(ዶ/ር)፤ ከተማዋን ወደ ስማርት ሲቲ የመቀየርና ከ2 መቶ 53 በላይ ፕሮጀክቶች መሰራታቸውን ተናግረዋል።

‎በንጹህ የመጠጥ ውሃ፣ በጤና፣ በትምህርት፣ በገቢ አሰባሰብና ስራ ፈጠራ የተለያዩ ስራዎች መሰራታቸውን ገልጸዋል።

‎የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዝናቡ ወልዴ(ዶ/ር) ባለፉት አምስት አመታት ብልጽግና ፓርቲ በውስብስብ ችግሮች ውስጥ እያለፈ ሀገርን በጠንካራ የተባበሩ ክንዶች እያሸጋገረ መሆኑን አመላክተዋል።

‎ፓርቲው ኢትዮጵያ በአፍሪካ ካሉ ሀገራት በኢኮኖሚ ወደ ከፍተኛ ደረጃ እንድትመጣ አስችሏል ያሉት ዶ/ር ዝናቡ፤ የስንዴ ልማታችን በምግብ ሰብል ራስን ከመቻል ባለፈ የሀገር ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ አስችሏል ብለዋል።

‎ባለፉት አመታት በዞኑ በቡና ልማትና ግብይት በእንሰት ልማት ኢኒሼቲቭ እንዲሁም በምግብ ራስን መቻል የተለያዩ ስራዎች ተሰርተው ውጤታማ መሆን መቻላቸውን ዶ/ር ዝናቡ ተናግረዋል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እና ስራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ ‎አበባየሁ ታደሰ(ዶ/ር)፤ የብልጽግና ፓርቲ የሉዐላዊነትና የአንድነት አለመጣጣም፣ ስር የሰደደ ድህነት፣ አውዳሚ ግጭትና ጦርነት፣ ዴሞክራሲያዊ የሆነ ስርዓት አለመኖርና የመሳሰሉ ችግሮችን አስወግዶ የሚጨበጥ ተስፋና ነገን በብቃት ለመተለም የሚያስችል ራዕይ ሰንቆ እየሰራ እንዳለ ገልጸዋል።

‎በፓርቲው መሪነት ለአመታት የተጓተቱ ፕሮጀክቶችን ከማጠናቀቅ ባለፈ የበጋ ስንዴና የሌማት ትሩፋት፣ በግብርና ምርትና ምርታማነት በማሳደግ በምግብ ሰብል ራሳችንን የመቻል ሁኔታን እያረጋገጥን እንገኛለን ሲሉ ዶ/ር አበባየሁ ተናግረዋል።

‎በሰላም ግንባታ፣ የተመጣጠነ ምግብ፣ ንጹህ የመጠጥ ውሃ፣ ፍትሐዊ የጤና እንክብካቤ ዜጎች እንዲያገኙ እንደሚሰሩ የተናገሩት ዶ/ር አበባየሁ፤ የትውልድ ልህቀትን ለማረጋገጥ የመምህራንን ህይወትና ጥቅማቸውን ለማሻሻል ፓርቲው ከመቼውም ጊዜ በበለጠ እንደሚሰራ ጠቁመዋል።

‎በድጋፍ ሰልፉ ከተገኙት መካከል መቅደስ ክፍሌና አቡሽ ሙንጣዝ፤ ሰላማዊ ምርጫ በማድረግ መንግስትን ማስቀጠል እንደሚገባ ተናግረዋል።


‎ዘጋቢ: ውብሸት ካሳሁን – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን