ግንቦት 24 በሚካሄደው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የሚወዳደሩ የብልጽግና ፓርቲ ዕጮዎችን የማስተዋወቂያ፣ የምረጡኝ ቅስቀሳ እና የድጋፍ ሰልፍ በደቡብ ኣሪ ወረዳ ጋዘር ከተማ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎችና የፓርቲው ዕጩዎች በተገኙበት ተካሂዷል።
የድጋፍ ሰልፉ ዋና ዓላማ በዞኑ በሁለት ምርጫ ክልል ለሚደረገው 7ኛ ጠቅላላ ምርጫ የብልጽግና ፓርቲን ይምረጡ የመጨረሻ ቅስቀሳ መርሃ-ግብርና ፓርቲው ባለፉት የለውጥ ዓመታት ያስመዘገባቸውን ትልልቅ ስኬቶች በመድገም ኢትዮጵያን ወደ ተምሳሌት ሀገር የማሸጋገር ግብን ዕውን ለማድረግ ያለመ ነው ተብሏል።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የወላይታ ሶዶ ክላስተር አስተባባሪ አማካሪና የሶዶ ክላስተር ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ተሰፋዬ ደፋሩ፤ በመድረኩ ለታዳሚው ባስተላለፉት መልዕክት ፓርቲው ባሳለፍናቸው ስምንት ተከታታይ አመታት የውጭም ሆነ የውስጥ ፈተናዎች በብቃት በመወጣት በርካታ ስኬቶችን ያስመዘገበ ፓርቲ መሆኑን በመግለጽ፤ የብልጽግና ፓርቲ የተረከባቸውን የፖለቲካና የኢኮኖሚ እዳዎችን በማስተካከል ሀገሪቱን ወደ ለውጥ ጎዳና ያሸጋገረና እያሸጋገረ ያለ ፓርቲ ነው ብለዋል።
የብልጽግና ፓርቲ ሀገሪቱን በሚረከብበት ጊዜ ብዙ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ቁስል ያለበትን ሀገር ተረክቧል ያሉት የኣሪ ዞን ብልጽግና ጽ/ቤት ኃላፊና ዋና የመንግሥት ተጠሪ እና የክልል ምክር ቤት ዕጩ ተወዳዳሪ አቶ አፈዶ ወርቁ በበኩላቸው፤ ትላንትን በማከምና ነገን በመተንተን ኢትዮጵያን ወደ ተምሳሌት ሀገር ለማሻገር ትልቅ ራዕይ ይዞ እየተጓዘ ያለ በመሆኑ ሁሉም ህዝብ ወዶና ፈቅዶ ብልጽግናን እንዲመርጥ ጥሪ አቅርበዋል።
የጋዘር ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ በለጠ ማጎ፤ በወረዳው ከሚገኙ ሁሉም ማህበረሰብ ጋር በተቀናጀ መልኩ በትብብር በመስራት ለተሻለ ለውጥና ልማት የብልጽግና ፓርቲን በመምረጥ የዞኑ ህዝብ ውክልናውን እንዲያጠናክርም ጠይቀዋል።
በዞኑ በተለያዩ አካባቢዎች በተመሳሳይ መልኩ የድጋፍ ሰልፎች ሲካሄዱ መቆየታቸውን የሚገልጹት የፓርቲው አባላትና ደጋፊዎች፤ ምርጫውን ሠላማዊ በሆነ መንገድ ለማጠናቀቅ ዝግጅት ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
የብልጽግና ዕጩ ተወዳዳሪዎችም በመድረኩ ተገኝተው የምረጡን ቅስቀሳ በማካሄድ መርሃ- ግብሩ ተጠናቋል።
ዘጋቢ: ጄታ ታገሠ – ከጂንካ ጣቢያችን

More Stories
ወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የእርስ በርስ ግንኙነትና አንድነትን የሚያጠናክር ተግባር መሆኑ ተገለጸ
በክልሉ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ የተጀመሩ ተግባራት ተጠናክረው መቀጠል አለባቸዉ – ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ
የሕዝባችንን የልማት ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ የመመለስና ሜጋ ፕሮጀክቶችን በፍጥነት የማጠናቀቅ ቁርጠኝነታችንን አጠናክረን እንቀጥላለን-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)