‎የሀገራችንን ብልፅግና እውን ለማድረግ በበቂ ዕውቀትና ክህሎት የታነፁ ምሁራንን በማፍራት የተሻለ ትውልድ መቅረጽ ቁልፍ ተግባር ነው ሲሉ የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዝናቡ ወልዴ(ዶ/ር) ገለፁ

‎የሀገራችንን ብልፅግና እውን ለማድረግ በበቂ ዕውቀትና ክህሎት የታነፁ ምሁራንን በማፍራት የተሻለ ትውልድ መቅረጽ ቁልፍ ተግባር ነው ሲሉ የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዝናቡ ወልዴ(ዶ/ር) ገለፁ

‎አስተዳዳሪው ይህንን ያሉት መሠረት መኩሪያ ፋውንዴሽን ባለፉት ሁለት ዓመታት “ሺህ ዶክተሮችን እናፈራለን” በሚል መሪ ቃል በትምህርት ዘርፍ ለሠራው ተግባር ከአሜሪካ መንግስት የተሰጠው እውቅና ማብሰሪያ መርሃግብር በዲላ ከተማ በተካሄደበት ወቅት ነው።


‎በመርሃግብሩ እንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት የመሠረት መኩሪያ ፋውንዴሽን ሥራ እስኪያጅ አቶ ኤልያስ አዶላ፤ ፋውንዴሽኑ የተማረ የሰው ሀይል የማፍራት ራዕይ አንግቦ ከ2016 ዓ.ም ጀምሮ 24 የሚሆኑ ተማሪዎችን በተለያዩ ዩነቨርሲቲዎች በዶክትሬት ዲግሪ እያስተማረ ይገኛል ብለዋል።

‎በቀጣይ ፋውዴሽኑ በትምህርት ዘርፍ ምሁራንን ለማፍራት ከሚያደርገው ተግባር በተጨማሪ በበጎ አድራጎትም ለመሳተፍ ዕቅድ ነድፎ እየሠራ መሆኑን ሥራ እስኪያጁ ጠቁመዋል።

‎ ፋውንዴሽኑ በኢፌዲሪ ፍትህ ሚነስቴር ህጋዊ ሰውነት አግኝቶ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን የተናገሩት አቶ ኤልያስ፤ ከዚህም ባሻገር በቅርብ ጊዜ በአሜሪካ ባሉ የአካባቢ ተወላጆች በሆኑ ዲያስፖራዎች አማካኝነት ከአሜሪካ መንግሥት በኩል እውቅና ማግኘቱ የበለጠ ለሥራ እንደሚያነሳሳቸው አስረድተዋል።

‎በመርሃ ግብሩ ላይ ንግግር ያደረጉት የፋውንዴሽኑ ፕሬዚዳንት ወ/ሮ ምስጋና ዋቃየሁ፤ የተማረ ሰው ሀይል በማፍራት ለዞኑ ብሎም ለሀገር ሁለተናዊ ዕድገት ሚናውን የመወጣት ዓላማ ሰንቆ የተነሳው ፋውንዴሽኑ ዛሬ ላይ የሚታዩና የሚጨበጡ ለውጦች ማስመዝገቡን ገልፀዋል።

‎ፋውንዴሽኑ በኢኮኖሚ አቅም ማነስ መማር ያልቻሉ ተማሪዎችን በማስተማር በትምህርት ዘርፍ ከመንግስት ጎን በመቆም እየሠራ መሆኑን የገለፁት ፕሬዚዳንቷ፤ ሁሉም አካላት ፋውንዴሽኑን በገንዘብና በዕውቀት በመደገፍ የሚጠበቅባቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

‎በመርሃግብሩ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳደሪና የመሠረት መኩሪያ ፋውንዴሽን የበላይ ጠባቂ ዝናቡ ወልዴ(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የሀገራችንን ብልፅግና እውን ለማድረግ በበቂ ዕውቀትና ክህሎት የታነፁ ምሁራንን በማፍራት የተሻለ ትውልድ መቅረጽ ቁልፍ ተግባር መሆኑን ተናግረዋል።

‎በትምህርትና በበጎ አድራጎት ሰፊ ተሳትፎ እያደረገ ያለውን መሠረት መኩሪያ ፋውንዴሽን በቀጣይም የዞኑ አስተዳደር በሚያስፈልገው ከጎኑ በቁርጠኝነት እየሠራ መሆኑን ገልፀዋል።

‎ካነጋገርናቸው በፋውንዴሽኑ የ3ኛ ዲግሪ ትምህርት ዕድል አግኝተው እየተማሩ ካሉ ተማሪዎች መካከል አዳነ በቀለና ሠራዊት ኤልያስ፣ የትምህርት ፍላጎት እያላቸው በኢኮኖሚ አቅም ማነስ ለዓመታት ሳይማሩ መቅረታቸውን ጠቁመው ፋውንዴሽኑ በሰጠው ዕድል መደሰታቸውን ተናግረዋል።

‎በመጨረሻም ለፋውንዴሽኑ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃግብር ተካሂዷል፡፡

‎ዘጋቢ፡ ዘርሁን ሹፌር – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን