የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አባል መሆናቸው ከብዙ ህክምና ወጪ የታደጋቸው መሆኑን በወላይታ ዞን የኪንዶ ዲዳዬ ወረዳ ሃላሌ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ተገልጋዮች ተናገሩ
የኪንዶ ዲዳዬ ወረዳ ጤና ጽህፈት ቤት በበኩሉ ሆስፒታሉን ጨምሮ በሁሉም ጤና ተቋማት ለተገልጋዮች አቅም በማይጎዳ መልኩ የተሻለ አገልግሎት ለመሰጠት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ቅንጅታዊ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አሰታውቋል፡፡
በወረዳው ቦሳ ቦርቶ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አቶ ተስፋዬ አሻንጎ እና ወ/ሮ አየለች አድማሱ፤ የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አገልግሎት ተጠቃሚዎች ሲሆኑ በየጊዜው እየተሰጠ ያለውን የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት ተግባራዊ በማድረግ ከብዙ ወጪ መትረፋቸውን ገልጸዋል።
ሌላኛው አሰተያየት ሰጪ በወረዳው ሲሜ ዶላየ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አቶ አሻ አላንቦ እኛ ወ/ሮ ጣብታ ዳጳሳ፣ የማአጤመ አባል በመሆን በየዓመቱ አንድ ጊዜ በማሳደስ ያለምንም ተጨማሪ ክፍያ በሆስፒታሉ ነፃ የህክምና አገልግሎት በማግኘት ራሳቸውንና ቤተሰቦቻቸውን ከከፍተኛ ወጪ መታደግ መቻላቸውን አስረድተዋል።
ይህ አገልግሎት ለቀጣይም ጠንክሮ እንዲቀጥልና ሌሎችንም ተጠቃሚ ከማድረግ አንጻር ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ትኩረት እንዲሰጥ ጠይቀዋል።
በሆስፒታሉ የካርድ ክፍል አገልግሎት አሰተባባሪ የሆኑት ወ/ሮ መሠረት ሻንካ እንደሚሉት፤ የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አገልግሎት ተጠቃሚዎች በርካታ መሆናቸውንና ለተገልጋዮች ያለምንም ልዩነት ቀልጣፋ አገልግሎት ይሰጣል።
በወረዳው የላሌ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ሥራ አስኪያጅ አቶ ማቲዮስ መንገሻ በበኩላቸው፤ ለማህበረሰቡ የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት ከዚህ በፊት ሲነሳ የነበረው የመድኃኒት አቅርቦትና የህክምና ቁሳቁስ ክፍተት ተሟልቶ ኤክስሬይ ማሽን ወደ ሰራ መግባቱን ጠቁመዋል።
አክለውም የማአጤመ አባል የሆኑትን ያለምንም መጨናነቅ ሆስፒታሉ ነፃ አገልግሎት ከመሰጠቱ ባለፈም ከአጎራባች ወረዳዎች ጋር ተፈራርሞ ለማህበረሰቡ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን አሰረድተዋል።
በወረዳው ጤና ጽ/ቤት ማአጤመ አገልግሎት አሰተባባሪ አቶ ታደለ ታዲዮሰ እንደሚሉት፤ በወረዳው ጎጮ፣ ሸላ ሳዴ ጤና ጣቢያና በሃላሌ ሆስፒታል አስከአሁን ከ13 ሺ 500 በላይ የማህበረሰብ ክፍሎች አገልግሎት አግኝተዋል።
ሆስፒታሉን ጨምሮ በሁለቱም ጤና ተቋማት ለተገልጋዮች አቅም በማይጎዳ መልኩ የተሻለ አገልግሎት ለመሰጠት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ቅንጅታዊ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የኪንዶ ዲዳዬ ወረዳ ጤና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ መልካሙ ሄልሶ አመላክተዋል።
ጨምረውም ከዚህ በፊት ከመድኃኒት አቅርቦት ጋር በተያያዘ ሲነሱ የነበሩ ችግሮችን ለመቅረፍ ቅድመ ቁርጥ ክፍያ በዓመት ሁለት ጊዜ በመፈራረም በአሁኑ ሰዓት ሆስፒታሉን ጨምሮ በሁሉም ጤና ተቋማት ተገልጋዮች በቂ አገልግሎት እያገኙ መሆናቸውን አስረድተዋል።
ዘጋቢ፡ ያሲን ጨተላ – ከዋካ ጣቢያችን

More Stories
የሀገራችንን ብልፅግና እውን ለማድረግ በበቂ ዕውቀትና ክህሎት የታነፁ ምሁራንን በማፍራት የተሻለ ትውልድ መቅረጽ ቁልፍ ተግባር ነው ሲሉ የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዝናቡ ወልዴ(ዶ/ር) ገለፁ
ተፈላጊነቱ እየጨመረ የመጣውን የቆጮ ምግብ ጥራትና ተደራሽነት ከፍ ለማድረግ የሚያስችሉ የምርምር ስራዎች እያከናወነ መሆኑን በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የብሔራዊ ግብርና ባዮ ቴክኖሎጂ ምርምር ማዕከል ገለጸ
በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚከበረው የአህዮች ቀን በጎፋ ዞን ሳውላ ከተማ ተከበረ