የህዝቡን መሰረታዊ ፍላጎት ለማሟላት የብልጽግና ፓርቲ ከምንጊዜውም በላይ እየሰራ እንደሚገኝ ተገለጸ

የህዝቡን መሰረታዊ ፍላጎት ለማሟላት የብልጽግና ፓርቲ ከምንጊዜውም በላይ እየሰራ እንደሚገኝ ተገለጸ

‎ሀዋሳ፡ ግንቦት 15/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) የህዝቡን መሰረታዊ ፍላጎት ለማሟላት የብልጽግና ፓርቲ ከምንጊዜውም በላይ እየሰራ እንደሚገኝ የክልል ምክር ቤት እጩ ተወዳዳሪና የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከተማ እና መሰረተ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ብርሃኑ ዘውዴ ገለጹ።

‎በአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ የኦቾሎ ክላስተር “ኢትዮጵያን ወደ ተምሳሌት ሀገር” በሚል መሪ ቃል የብልጽግና ፓርቲ የምርጫ ቅስቀሳና ህዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ ተካሂዷል።

‎በመድረኩ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የክልል ምክር ቤት እጩ ተወዳዳሪና የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከተማ እና መሰረተ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ብርሀኑ ዘውዴ፤ ብልጽግና ሰው ተኮር ፓርቲ በመሆኑ ቀዳሚና ዋነኛ ግቡ የሰው ልጅ ተጠቃሚነት ነው።

‎ኢትዮጵያን በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ውስጥ በአፍሪካ በምሳሌነት የምትጠቀስ እና በዓለም ካሉ የተሻሉ አገራት ተርታ እንድትሰለፍ ለማድረግ ፓርቲው በትጋት እየሰራ እንደሚገኝ የገለጹት አቶ ብርሀኑ፤ ለዚህም ትልቁ ማሳያ የህዳሴ ግድባችን አንዱ መሆኑን ጠቁመዋል።

‎ፓርቲው አገሪቱን ወደተሻለና ከፍ ያለ ደረጃ ለማድረስ አቅዶ የተነሳ በመሆኑ መጪውን ምርጫ አስመልክቶ ህዝቡ የብልጽግና ፓርቲ የምርጫ ምልክት የሆነውን “የስንዴ ነዶ” እንዲመርጥ ጥሪ አቅርበዋል።

‎የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ደምሴ አድማሱ በበኩላቸው፤ ብልጽግና ፓርቲ በሀገር አቀፍ ደረጃ ታላላቅ ድሎችን እያስመዘገበ መሆኑን ገልጸዋል።

‎አርሶ አደሩን ቀጥተኛ ተጠቃሚ የሚያደርጉ በርካታ የልማት ፕሮጀክቶች በስኬት እየተከናወኑ እንደሚገኙም አብራርተዋል።

‎ኢትዮጵያን ወደተሻለ የዕድገት ምዕራፍ ለማሸጋገር እየተሰራ መሆኑን የጠቆሙት ዋና አስተዳዳሪው፤ ህዝቡ ግንቦት 24 ቀን በሚካሄደው ምርጫ የስንዴ ነዶን በመምረጥ ድጋፉን እንዲያረጋግጥ ጠይቀዋል።

‎የአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዳዊት ታደሰ፤ ብልጽግና ፓርቲ ሀገርን ከመበታተን አደጋ ታድጎ ወደተሻለ የሰላምና የልማት ምዕራፍ እያሻገራት እንደሚገኝ አስገንዝበዋል።

‎የሕዝብን ተጠቃሚነት በዘላቂነት ለማረጋገጥ በሚደረገው ጉዞ ውስጥ ህዝቡ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያበረክትና በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የብልጽግና ፓርቲን በመምረጥ የሀገሪቱ የለውጥ ጉዞ እንዲፋጠን የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

‎በድጋፍ ሰልፉ ላይ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ የጋሞ ዞን፣ የአርባ ምንጭ ከተማ እና የወረዳው ከፍተኛ አመራሮች፣ የፓርቲው አባላት እንዲሁም በርካታ ቁጥር ያላቸው የአካባቢው ነዋሪዎች የተሳተፉ ሲሆን በመርሃ ግብሩ የፓርቲው አላማና መርሆችን በማቅረብ ተካሂዷል።

ዘጋቢ: ገነት መኮንን – ከአርባ ምንጭ ጣቢያችን