ኢትዮጵያ የሚገጥሟትን የህልውና ፈተናዎች በመሻገር ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማሳካት የሚያስችል ሀገራዊ ፓርቲ ገንብታለች – ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ

ሀዋሳ፡ ግንቦት 14/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) ኢትዮጵያ የሚገጥሟትን የህልውና ፈተናዎች በመሻገር ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማሳካት የሚያስችል ሀገራዊ ፓርቲ መገንባቱን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ አስታወቁ።

ርዕሰ መስተዳድሩ በተገኙበት የብልጽግና ፓርቲ የምርጫ ቅስቀሳ እና ህዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ በጋሞ ዞን በተለያዩ አካባቢዎች እንደቀጠለ ነው።

በዞኑ ዲታ ወረዳ ዛዳ ከተማ በተካሄደው መርሃ ግብር የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ፣ የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ደምሴ አድማሱን (ዶ/ር) ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የክልል፣ የዞን፣ የፓርቲው ዕጩ ተመራጮች፣ ምሁራንና ሌሎች በተገኙበት የምርጫ ቅስቀሳው በደማቅ ሁኔታ ተካሂዷል።

በዚህ የቅስቀሳ መድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አሸናፊ ኦይዳ (ዶ/ር) እንዳሉት፤ ወረዳው የዘመናት የመንገድ ጥያቄን የግርጫ ዋጫ ደረጃውን የጠበቀ የኮንክሪት አስፓልት በመሥራት ምላሽ እንደዲያገኝ ተደርጓል።

የትምህርትና የጤና ዘርፎች ምላሽ እንዲያገኙ በማድረግ እንዲሁም የዛዳ ከተማ የመንገድ ዳር መብራት ከ26 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ አገልግሎት እንዲያገኝ በማስቻል የለውጡ መንግስት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማድረጉንም አስታውሰዋል።

የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ደምስ አድማሱ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ብልፅግና ፓርቲ የጀመረውን መጨረስ የሚችል የህዝቦችን ተጠቃሚነትን ባለፉት ስምንት አመታት ያረጋገጠ መሆኑን ጠቅሰው የተጀመሩትን ግዙፍ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎችን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላፉት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ፤ የአካባቢው ህዝብ ለዘመናት ሲያነሳ የነበረውን የመሠረተ ልማት ጥያቄ ደረጃ በደረጃ እየመለሰ የቆየው ሰው ተኮር የሆነው የብልፅግና ፓርቲ መሆኑን ተናግረዋል።

በይበልጥ የአካባቢው አርሶ አደር ያመረተውን ምርት ለገበያ ለማቅረብ ብሎም ከአቻ ወረዳዎች ጋር እንዳይገናኝ ፈተና የነበረውን መንገድ ደረጃውን በጠበቀ አስፋልት በመገንባት በአጭር ጊዜ ውስጥ ምላሽ መሰጠቱ የፓርቲውን አገልጋይነት የሚያመላክት ነው ብለዋል።

ብልፅግና ጀመሮ የመጨረስ ብሎም አዳዲስ ፕሮጀክቶችን የሚጀምር የገባውን ቃል የሚያከብር ፓርቲ መሆኑንም አፅንኦት ሰጥተውበታል።

ኢትዮጵያ የአለም ተምሳሌት ማሳያ የህዝቦቿን ብልፅግና ማረጋገጥ የቻለች መሆኗን ያስመሠከረ ፓርቲ መሆኑን ያስታወሱት ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ፤ ይህንን ፓርቲ መምረጥ ከድህነት መላቀቅና ብልፅግናን ማረጋገጥ ነውም ብለዋል።

ምርጫው ፍፁም ሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቅ የክልሉን መገለጫ የሆነውን ሠላም ማረጋገጥ ይገባል ሲሉ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።

የፓርቲው የመወዳደሪያ ምልክት የሆነው የስንዴ ነዶ አቃፊነትን፣ አንድነትንና የጋራ ስኬትን አመላካች ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ባለፉት ስምንት ዓመታት የተገኙ ሀገራዊና ክልላዊ ድሎች የአንድነታችን ውጤት ነው ብለዋል፡፡

አቶ ጥላሁን አያይዘውም፤ በሀገሪቱ ብሎም በክልሉ የተመዘገቡ አመርቂ ውጤቶችን ለማስጠበቅና የተጀመሩ ሰው ተኮር ተግባራትን ለማስቀጠል የስንዴ ነዶን በመምረጥ ኢትዮጵያን ወደ ብልጽግና ማማ ማሻገር እንደሚገባ ጠቁመዋል።

ዘጋቢ፡ በኃይሉ ሙሉጌታ – ከአርባምንጭ ጣቢያችን