ክልሉን የኢንዱስትሪ ማዕከል ለማድረግ እየተሰራ ነው – አቶ ስንታየሁ ወልደሚካኤል
ክልሉን የኢንዱስትሪ ማዕከል ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የከተማና ኢንዱስትሪ ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ስንታየሁ ወልደሚካኤል ገለጹ።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን በከምባታ ዞን በዱራሜ እና በሺንሺቾ ከተማ በ90 ሚሊዮን ብር ወጪ ያስገነባቸውን የማምረቻ ኢንዱስትሪ ሼዶችን አስመርቋል።
ኢንዱስትሪ ምርትን፣ አገልግሎትን፣ የስራ እድልን፣ የውጭ ምንዛሪን፣ የቴክኖሎጂ ሽግግርን በአንድ ማዕከል አካቶ የያዘ ዘርፍ መሆኑን በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የከተማና ኢንዱስትሪ ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ስንታየሁ ወ/ሚካኤል ተናግረዋል።
ኢንዱስትሪው በአንድ ዘርፍ ተንጠልጥሎ የነበረውን የኢኮኖሚ ፖሊሲ ወደብዝሃ ዘርፍ በማምጣት እየሰፋ ያለ ዘርፍ ስለመሆኑም አክለዋል።
ክልሉ በግብርና ምርቶች እና በተፈጥሮ ጸጋም የታደለ ከመሆኑም በተጨማሪ ለማዕከላዊ የገበያና ለወደብ አቅራቢያ ላይ የሚገኝ መሆኑ ትልቅ ዕድል መሆኑን ተናግረዋል።
መንግስት ለገጠሩ ሽግግር አቅዶ እየሰራ መሆኑን የገለጹት አቶ ስንታየሁ የአርሶ አደሩን ምርት እሴት በመጨመር ጥራት ያለውን ምርት ለገበያ ለማቅረብ የኢንዱስትሪ ማዕከላት መስፋፋት ወሳኝ ስለመሆኑም አሰረድተዋል።
ክልሉን ኢንዱስትሪ ማዕከል ለማድረግ እየተሰራ ስለመሆኑም አሳውቀዋል።
የክልሉ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ናትናኤል ሚሊዮን በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ኮርፖሬሽኑ በክልሉ በአስር ከተሞችና በ15 ሳይቶች የተለያዩ አምራቾችን እያስተዳደረ የሚገኝ ሲሆን መሰረተ ልማቶችን በመዘርጋትና ለአምራቾች በማስተላለፍ የውጭ ምንዛሪ የሚያስገኙ ተኪ ምርቶች እንዲመረቱ፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲደረግ እንዲሁም የስራ እድል እንዲፈጠር እየሰራ ይገኛል።
በአሁኑ ጊዜ በክልሉ የሼዶችን ቁጥር ወደ 1 መቶ 70 ማድረስ ተችሏል ያሉት አቶ ናትናኤል፤ ዘርፉም ክልሉን የአምራች ኢንዱስትሪ ማዕከል ለማድረግ የተቀመጠውን ግብ የሚያሳካ ነው ብለዋል።
ኮርፖሬሽኑ ያለውን የተፈጥሮ ሀብት፣ የሰው ኃይልና የግብርናውን እምቅ አቅም ከኢንዱስትሪ ጋር በማስተሳሰር ክልሉን የማምረቻና የኢንዱስትሪ ማዕከል የማድረግ ተልዕኮውን እየተወጣ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
የከምባታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አረጋ እሸቱ በበኩላቸው፤ መንግስት የሀገሪቱን ሁለንተናዊ ብልጽግና ለማረጋገጥ በተለይ ግብርናውን ከኢንዱስትሪ ጋር አስተሳሰሮ እየሰራ በሚገኝበት ወቅት ሼዶቹ መገንባታቸውን ተናግረዋል።
ዘርፉ የአርሶ አደሩ ምርት እሴት ተጨምሮበት እንዲቀርብ ትልቅ አቅም ነው ብለዋል።
በዘርፉ የመሰማራት ፍላጎት ያላቸው ባለሃብቶች ሼዱን እንዲጠቀሙ የተመቻቸውን ዕድል እንዲጠቀሙ ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ: ኤርጡሜ ዳንኤል – ከሆሳዕና ጣቢያችን

More Stories
የብልፅግና ፓርቲ የምርጫ ቅስቀሳና ዞን አቀፍ ማጠቃለያ ህዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ በሸካ ዞን ቴፒ ከተማ እየተካሄደ ነው
የብልጽግና ፓርቲ አዳዲስ ኢኒሼቲቮችን በመፍጠር የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ በርካታ የልማት ሥራዎችን እየተገበረ ይገኛል – አቶ አንተነህ ፈቃዱ
የጂንካ ከተማ አስተዳደር የኦንላይን ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት መስጫ ማዕከል በይፋ ስራ ጀመረ