ዜጎች ሠላማቸው ተጠብቆ በነጻነት ምርጫን ማካሄድ እንዲችሉ ፖሊስ እየሠራ መሆኑ ተገለጸ

ዜጎች ሠላማቸው ተጠብቆ በነጻነት ምርጫን ማካሄድ እንዲችሉ ፖሊስ እየሠራ መሆኑ ተገለጸ

‎ግንቦት 24 የሚካሄደው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሠላማዊ እንዲሆን የሚያስችል ስልጠና ለሸካ ዞን ፖሊስ፣ ለቴፒ ከተማ እና የኪ ወረዳ አመራሮች እና አባላት በቴፒ ከተማ ተሰጥቷል።

‎7ኛ ጠቅላላ ምርጫ በሰላም እንዲካሄድ የፖሊስ ሚና ከፍተኛ መሆኑን በስልጠና ወቅት የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የሸካ ዞን ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ኮማንደር አስታወሰኝ አይሞ እንዳሉት፤ በምርጫ ወቅት የሚፈጠሩ አለመግባባቶች እና ግጭቶችን ሙያዊ ዲሲፕሊን በጠበቀ መልክ አባሉ በቁርጠኝነት ሊወጣ ይገባል።

‎አባላቱ ስልጠናውን በአግባቡ በመከታተል እስከ ድህረ ምርጫ ድረስ ለተግባራዊነቱና ለሙያቸው ትኩረት በመስጠት ሊዘጋጁ እንደሚገባና ወደታችኞቹ መዋቅሮች ጭምር ማውረድ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

‎የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ረዳት ኮሚሽነር አለሙ ዳሾ በበኩላቸው፤ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ፖሊስ እንደ ህዝብ መራጭ፣ እንደ ፖሊስ ደግሞም ጸጥታ አስከባሪ በመሆን ራሱን እንዲያዘጋጅና የዞኑን ሠላም ለማስጠበቅ አባሉ በአንድነትና በተጠንቀቅ መዘጋጀት አለበት ነው ያሉት።

‎እያንዳንዱ ዜጋ የዲሞክራሲያዊ መብቱን ተጠቅሞ በነጻነት ምርጫን መምረጥ እንዲችል የፖሊስ ሚና ላቅ ያለ በመሆኑ በምርጫ ህግጋት ማዕቀፎች እና እስከ ድህረ ምርጫ ድረስ የጸጥታ አካላት ህገመንግስታዊ መብቶችን አስመልክቶ የተዘጋጀ ሰነድ በሸካ ዞን ፖሊሲ መምሪያ የህዝብ ግንኙነትና የፀጥታ ግንባታ ዲቪዥን ኃላፊ ኮማንደር ልሳነወርቅ ተስፋዬ ቀርቧል።

‎ዜጎች ዲሞክራሲያዊ ምርጫ እንዲያካሂዱ ፖሊስ የተለያዩ ጥቃቶችንና ግጭቶችን እየተከላከለ የህግ የበላይነት እንዲከበር እና በምርጫ ወቅት የህዝብ አመኔታ እንዲኖር ማድረግ እንደሚጠበቅበት ኮማንደር ልሳነወርቅ አንስተዋል።

‎ምርጫ ሰላማዊ ሆኖ ከተጠናቀቀ ለፖሊስ አመራርና አባላት ትልቅ ኩራት እንደሆነ በሰነዱ መነሻ ከአባላቱ አስተያየት የቀረበ ሲሆን በዚህም የሀገር ደህንነትን በማስጠበቅ የህዝቡን ስጋት ፈጥነው ለመረዳት የሚያግዝ ስልጠናን ከመድረኩ ማግኘታቸውን ገልጸዋል።

‎የ7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ ደህንነት ከማጠበቅ
‎ባሻገር የምርጫ ቁሳቁሶችን፣ መራጮችንና፣ አስመራጮችን በንቃት መከታተል ላይ ትኩረት እንደሚያደርጉም አንስተዋል።

‎በምርጫ ወቅት ፖሊስ መቼና እንዴት ሀይል መጠቀም እንደሚችል የተገለጸ ሲሆን ሰነዱን መነሻ በማድረግ ከተሳታፊዎች አስተያየቶችና ጥያቄዎች መነሻ ቀርቦ ከአመራሩ ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቷል።

‎የዘንድሮው ምርጫ ስኬት ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአፍርካና ለአለም አቀፍ ተቋማት ጭምር አርአያ መሆን እንዲችል እየተሰራ መሆኑን የገለጹት የሸካ ዞን ሠላምና ፀጥታ መምሪያ ሀላፊ አቶ ዋስሁን አውሎ፤ በዚህ መሠረት በየደረጃው የሚገኙ የጸጥታ አካላት በኃላፊነትና በተጠያቅነት ጭምር ሊመሩ ይገባል ብለዋል።

‎በዞኑ የሚገኙ ሁሉም የምርጫ ጣቢያዎች እስከአሁን ለምርጫ ብቁና ዝግጁ መሆናቸውንና ከዚህም በኋላ ይህ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የጸጥታ ኃይሉ ሚና የጎላ ስለመሆኑም ገልጸዋል።

‎በስልጠና መድረኩ ላይ የየመዋቅሩ የፀጥታ አመራሮች ፣ የፖሊስ አመራሮች እና አባላት ተሳትፈዋል።

‎ዘጋቢ: ታሪኩ ታደሰ – ከማሻ ጣቢያችን