የወላይታ ዞን የፍትህ አካላት 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሠላማዊ ሆኖ በስኬት እንዲጠናቀቅ የሕግ የበላይነትን የማስከበርና የዜጎችን መብት የማስጠበቅ ታሪካዊ ኃላፊነት እንዳለባቸው ተጠቆመ

የወላይታ ዞን የፍትህ አካላት 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሠላማዊ ሆኖ በስኬት እንዲጠናቀቅ የሕግ የበላይነትን የማስከበርና የዜጎችን መብት የማስጠበቅ ታሪካዊ ኃላፊነት እንዳለባቸው ተጠቆመ

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ፍትህ ቢሮ ኃላፊ አቶ ሙሉቀን ታደሰ በመድረኩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፤ “ምርጫ የዲሞክራሲ መገለጫ እንደመሆኑ ይህ ሂደት በስኬት እንዲጠናቀቅ የፍትህ አካላት የሕግ የበላይነትን የማስከበርና የዜጎችን መብት የማስጠበቅ ታሪካዊ ኃላፊነት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የቅድመ፣ የምርጫ ዕለትና ድህረ ምርጫ ወቅት የፖሊስ፣ ዐቃቤ ህግ፣ የሠላምና ፀጥታና ፍርድ ቤቶች ፍትህ የማስፈን ሚና የጎላ መሆኑን አንስተው፤ ምርጫ የሀገረ መንግሥት ግንባታ ምሰሶ ከመሆኑ አንጻር የፍትህ ተቋማት ገለልተኝነት የተጠበቀ እንደሆነም ጠቁመዋል።

በምርጫ ወቅት ወንጀሎች ሲከሰቱ ሰብአዊ መብት በማይጋፋ መንገድ እንዲሆን ያሳሰቡት የወላይታ ዞን ፍትህ መምሪያ ኃላፊ አቶ ጸጋው ስሞኦን፤ የፀጥታ አካላት ገለልተኛ እንዲሆኑና ግንዛቤ እንዲኖራቸው ለማድረግ ሥልጠናው ወሳኝ መሆኑን ነው የገለፁት።

የምርጫ ወንጀሎችን በመለየት ፈጣን ፍትህ እንዲሰጥ ጊዚያዊ ችሎት መዘጋጀቱን ያነሱት ኃላፊው፤ ምርጫው ነጻና ፍትሃዊ እንዲሆን የፍትህ ተቋማት ቁርጠኝነት ወሣኝ መሆኑን አክለዋል።

ሀሰተኛና የጥላቻ ንግግር በማህበራዊ ሚዲያ በድህረ ምርጫ ወቅት በምርጫ ቦርድ ያልተገለፀ የምርጫ ውጤት በሚያሰራጩ ግለሰቦችና የሚዲያ ተቋማት በትብብር ተጠያቂ ለማድረግ ሥራዎች በትኩረት እየተሠሩ እንደሆነም አስረድተዋል።

የምርጫ ቦርዶ አዋጅን መሠረት በማድረግ የጸጥታ አካላት ሕጉን በተከተለ መንገድ ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የፍትሕ ተቋማት ምርጫውን በሕግ አግባብ እንዲያከናውኑ ሥልጠናው አቅም እንደሚፈጥር አስተያየታቸውን የሰጡት የቦሎሶ ሶሬ ወረዳ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ወንድሙ ታምሬ፤ በምርጫ ሂደት የሚከሰቱ የወንጀል ድርጊቶችን ተጠያቂ ለማድረግ እንደሚሰራ አስረድተዋል።

የአረካ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አክሊሉ አብርሃም በበኩላቸው፤ ዜጎች ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን እንዲጠቀሙ ለማድረግ የምርጫ ሂደት እንዳይደናቀፍ በጊዜያዊ ችሎት ዳኞችን የመመደብ ሥራ መሰራቱን አስረድተዋል።

በመድረኩ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ፍትህ ቢሮ ኃላፊ፣ የወላይታ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት፣ የወላይታ ዞን ፍትህ መምሪያ ኃላፊ፣ የወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች ፍትህና ፍርድ ቤት የሥራ ኃላፊዎች እና የፍትህ አካላት ተገኝተዋል።

ዘጋቢ፡ ድርሻዬ ጋሻው – ከዋካ ጣቢያችን