የምሁር ኢየሱስ ገዳም የቱሪስት ፍሰቱን ለማሳደግና የምርምር ማእከል እንዲሆን መንግስት ባለሀብቱና ገዳሙ በትብብር መስራት አለባቸው – ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር)

ሀዋሳ፡ ግንቦት 12/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) የምሁር ኢየሱስ ገዳም የቱሪስት ፍሰቱን ለማሳደግና የምርምር ማእከል እንዲሆን መንግስት ባለሀብቱና ገዳሙ በትብብር መስራት እንደአለባቸው የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) በጉራጌ ዞን ምሁር አክሊል ወረዳ የምሁር እየሱስ ገዳምን ተመልክተዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት የምሁር እየሱስ ገዳም የረጅም ዘመናት የታሪክ ባለቤት ነው።

ገዳሙን የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ በልዩ ትኩረት መስራት ይገባል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ባለሀብቶች በገዳሙ ዙሪያ የእንግዶች ማረፊያ በመገንባት ለቱሪዝም ኢንዱስትሪው እድገት አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ አሳስበዋል።

ጎብኚዎች በገዳሙ የሚኖራቸውን የቆይታ ጊዜ ለማራዘም ምቹ ሁኔታ መፍጠር እንደሚገባም ርዕሰ መስተዳድሩ አብራርተዋል።

ገዳሙ ካለው የረጅም ዘመናት ሀይማኖታዊ ታሪክ አንጻር ለጥናትና ምርምር ስራዎች የሚኖረው አበርክቶ ከፍተኛ ስለመሆኑም ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል።

በየትኛውም የሀይማኖት ተቀቋማት የሚሰጠው መንፈሳዊ ትምህርት ትውልድ በማነጽ ረገድ ጉልህ ድርሻ እንዳለውም ርዕሰ መስተዳድሩ አብራርተዋል።

በገዳሙ ከመላው የሀገሪቱ ክልሎች የተውጣጡ የአብነት ተማሪዎች ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ስለመሆኑም ተመላክቷል።

የምሁር ኢየሱስ ገዳም በ13ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በጻድቁ አቡነ ዜና ማርቆስ የተመሰረተ መሆኑም ተጠቁሟል።

ገዳሙን የቱሪስት መዳረሻ በማድረግ ለጎብኚዎች ምቹ እንዲሆን ልዩ ልዩ የመሰረተ ልማት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የገዳሙ አባቶች አብራርተዋል።

በመስክ ምልከታው የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ሃላፊ አቶ ይግለጡ አብዛ፣

የክልል እና የዞን የስራ ሀላፊዎች እና ባለሀብቶች ተገኝተዋል።

ዘጋቢ፡ ሄኖክ ተክሌ – ከወልቂጤ ጣቢያችን