ከባዶነት ወደ እሳታማ ድባብ፦ ሚኬል አርቴታ የኤምሬትስን መንፈስ እንዴት ቀየረው?
በፈረንጆቹ ታህሳስ 2019 ሚኬል አርቴታ የለንደኑን ክለብ አርሰናልን ለመምራት በሩን ሲከፍት፣ ክለቡ ከተጫዋቾች መጫጫን በላይ ትልቅ በሽታ ነበረበት፦ ከደጋፊው ጋር ያለው ፍፁም መቆራረጥ!
የዛሬ 6 ዓመት ገደማ፣ አርቴታ የፔፕ ጋርዲዮላ ረዳት ሆኖ በኤምሬትስ ስታዲየም ማንቸስተር ሲቲ አርሰናልን 3 ለ 0 ሲያሸንፍ በዕለቱ ስታዲየሙ የነበረው ቅዝቃዜና 50 በመቶው ስታዲየም ባዶ መሆኑ ከአእምሮው አልጠፋም ነበር። “በዚህሁኔታውስጥምንምዓይነትፕሮጀክትመገንባትአይቻልም” ነበር ያለው ስፔናዊው ታክቲሻን።
ዛሬ ግን ያ ታሪክ ተረት ሆኗል። ኤምሬትስ አሁን የቅዠት ሳይሆን የጋለ እሳት መድረክ ሆናለች።
የአርሰናል ስታዲየም ድባብ በአንድ ጀምበር አልተቀየረም። መንገዱ እሾሃማ ነበር።
የኮቪድ-19 መከሰት ደጋፊን ለመመለስ ሲታሰብ ስታዲየሞች ሙሉ በሙሉ ዝግ ሆኑ።
የ2021-22 የውድድር ዘመን አስከፊ ጅማሮውም ይነሳል። ክለቡ የመጀመሪያዎቹን ሶስት ጨዋታዎች ተሸንፎ ከደረጃው ግርጌ ተቀምጦ ነበር።
ነገር ግን በዚያው አስቸጋሪ ወቅት የኖርዊች ጨዋታ ላይ ደጋፊዎች ያሳዩት “አብረን እንሰቃያለን” የሚል እምነት አርቴታን እንባ አራጭቶታል። ያቺ ዕለት የለውጡ መሰረት ነበረች።
አርቴታ ደጋፊዎችን “የቡድኑ 12ኛ ተጫዋች እና አስማተኛው ክፍል” ሲል ይጠራቸዋል።
በተለይ በዚህ የውድድር ዘመን የስታዲየሙ ድባብ ቡድኑን ወደ ሻምፒዮንነት እየገፋው ይገኛል።
የለውጡ ምስጢሮች ምን ምን ናቸው?
የወጣት ተጫዋቾች ዕድል ማግኘትና የአዳዲስ ፈራሚዎች ሚና ጉልህ ድርሻን ይወስዳል። እንደ ቡካዮ ሳካ እና ስሚዝ ሮው ያሉ የክለቡ አካዳሚ ውጤቶች፣ እንዲሁም እንደ ማርቲን ኦዴጋርድ፣ አሮን ራምስዴልና ዊሊያም ሳሊባ ያሉ ተጫዋቾች ደጋፊው ለቡድኑ ልዩ ፍቅር እንዲያድርበት አድርገዋል።
ሳሊባ በገዛ ጎሉ ላይ ባስቆጠረበት ዕለት ስታዲየሙ በጭብጨባ ሲያበረታታው የነበረው ትዕይንት ማሳያ ነው።
ሌላው የደጋፊዎች ንቅናቄ ነው። የቡድኑን ባስ (አውቶቡስ) በሺዎች የሚቆጠሩ ደጋፊዎች በጭስና በዝማሬ እንዲቀበሉ በማድረግ የስታዲየሙን ውጭ ገፅታ አነቃቅተውታል።
በተጨማሪም የአርቴታ ቀጥተኛ ጥሪዎች ተጠቃሾች ናቸው። አርቴታ በጋዜጣዊ መግለጫዎች ላይ ሳይቀር የጨዋታ ሰዓቶችን እየደጋገመ በመጥራት፣ ደጋፊዎች “ማለዳ ቁርስ በልተው” ስታዲየም እንዲገኙና “እውነተኛ መነሳሳት” ይዘው እንዲመጡ የሚሰጣቸው ትዕዛዞች ውጤት አምጥተዋል።
“ስታዲየሙ ያንን ያህል ጉልበት፣ ስሜት እና ተስፋ ሲያፈልቅ እሴቱ ማለቂያ የለውም። ቡድኑ ፍጹም የተለየ ይሆናል!” ሲሉ ሚኬል አርቴታ ይናገራሉ።
አርሰናል ላለፉት ሶስት ተከታታይ ዓመታት የፕሪሚየር ሊጉን ሁለተኛ ደረጃ ይዞ ቢያጠናቅቅም፣ በዚህ የውድድር ዘመን ግን ለየት ባለ ጭንቀት እና ተስፋ ውስጥ አልፏል።
በሜዳው ከፉልሃም ጋር ያደረገው ጨዋታ፣ እንዲሁም ከአትሌቲኮ ማድሪድ ጋር ለነበረው የቻምፒዮንስ ሊግ የግማሽ ፍፃሜ ድል የደጋፊው ድምፅ ወደር አልነበረውም።
እግር ኳስ በታክቲክና በገንዘብ ብቻ አይገነባም። ትልቁ ስኬት የሰዎችን ልብ ማሸነፍ ነው። አርቴታ በአርሰናል ያደረገው ትልቁ ተዓምር የጨዋታ አሸናፊነት ሳይሆን፣ የፈረሰውንና ቀዝቅዞ የነበረውን የኤምሬትስ ስታዲየም መንፈስ መልሶ ማቀጣጠሉ ነው።
ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ

More Stories
ክሪስቲያኖ ሮናልዶ ለ6ኛ ጊዜ በዓለም ዋንጫ ላይ ለመካፈል ተመረጠ!
የተፈጥሮ ማዳበሪያን በመጠቀም ከተሞችን ፅዱና ምቹ ከማድረግ ባሻገር የኤክስፖርት ምርትን ማሳደግ እንደሚያስፈልግ የአርባምንጭ ዩኒቨርስቲ ገለጸ
ወጣቶች የፊታችን ግንቦት ወር በሚካሄደው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ላይ የነቃ ተሳትፎ በማድረግ የዲሞክራሲ ባህል ማሳደግ እንደሚገባቸው በጌዴኦ ዞን የይርጋጨፌ ከተማ አስተዳደር ገለፀ