ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ለተመራቂ ተማሪዎቹ የተሻለ የስራ እድልና መነሳሳት ለመፍጠር በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ ገለፀ

ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ለተመራቂ ተማሪዎቹ የተሻለ የስራ እድልና መነሳሳት ለመፍጠር በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ ገለፀ

ዩኒቨርሲቲው ለሁለተኛ ጊዜ አመታዊ የስራ አውደ ርዕይ አካሂዷል።

የወልቂጤ ዩኒቨርቲ አካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት እና የዩኒቨርሲቲው ተወካይ ዶ/ር ሀብቴ ዱላ እንዳሉት፥ የአውደ ርዕዩ ተቀዳሚ ዓላማ ትስስር እና የትብብር ስሜትን በማሳደግ ከተቋሙ ለሚመረቁ ተማሪዎች የተሻለ የስራ እድልና መነሳሳት መፍጠር ነው።

ዩኒቨርሲቲው በመማር ማስተማር ስራዎች፣ በምርምር፣ በማህበረሰብ አገልግሎት እና ቴክኖሎጂን ከማሸጋገር በተጨማሪ ከኢንዱስትሪዎች ጋር ትስስር በመፍጠር ከውጥን እስከ ፍጻሜ በትጋት በመስራት አመርቂ ውጤቶች አስመዝግቧል ብለዋል።

በተቋሙ ተመራቂ ተማሪዎችን ከአንደኛ ዓመት ጀምሮ ከመደበኛው የመማር ማስተማር ስራ ባሻገር የህይወት ክህሎት ስልጠና እንዲያገኙ መደረጉን ተናግረዋል።

በአውደ ርዕዩ ተማሪዎች ከቀጣሪ ድርጅቶች ጋር በቀጥታ መገናኘታቸው፣ እንደ አንድ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ቀጣሪ ድርጅቶች እንደ ኢንዱስትሪ እና ተመራቂ ተማሪዎች ደግሞ እንደ ዕድሉ ተጠቃሚ በአንድ መድረክ መገናኘት ፋይዳው የጎላ እንደሆነም አብራርተዋል።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ስራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ ምክትልና የከተማ ስራ ዕድል ፈጠራ ዘርፍ ሀላፊ አቶ ታምራት ተስፋሁን በበኩላቸው የወልቂጤ ዩኒቨርቲ ብቁና ተወዳዳሪ ዜጎችን ከማፍራት ጎን ለጎን እንደ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ብሎም እንደ ሀገር እየተደረገ ያለውን ሁለንተናዊ ሽግግር ስኬታማ እንዲሆን አሻራውን በማሳረፍ ላይ ይገኛል ብለዋል።

ተቋማቸው ከሚያከናውናቸው ዘርፈ ብዙ ስራዎች መካከል የምሩቃን መዳረሻ ጥናት የስራ አውደ ርዕይ ማዘጋጀት ተጠቃሾች ናቸው ያሉት በዩኒቨርስቲው የትምህርት ጥራት ዳይሬክተር ረዳት ኘሮፌሰር ፋንታዬ ጨምር መሠል የስራ አውደ ርዕዮች በማሰናዳት ተመራቂዎችን ከቀጣሪ ድርጅቶች ጋር ማስተሳሰር በእጅጉ ጠቃሚ መሆኑን በመገንዘብ ተቋማቸው መርሃ ግብሩን ማዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡

የስራ አውደ ርዕዩ ተሳታፊ ተማሪዎች እና ቀጣሪ ድርጅቶች ዩኒቨርሲቲው ያዘጋጀው አመታዊ የስራ አውደ ርዕይ ጊዜ ገንዘብና ጉልበት ቆጣቢ በሆነ መንገድ ሠራተኛን ከአሰሪ ጋር የሚገናኝበት መልካም እድል በመሆኑ ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባው ጠቁመዋል።

የስራ አውደ ርዕዩ የትብብር ስሜትን በማሳደግ የተሻለ የስራ እድልና ብቃት ያላቸው ሙያተኞች በቀላሉ ከአሰሪ ድርጅቶች የሚገናኙበት በመሆኑ ተሞክሮውን ማስፋት እንደሚገባም አመላክተዋል አስተያየት ሰጪዎቹ ።

ዘጋቢ: ሪድዋን ሰፋ – ከወልቂጤ ጣቢያችን