ስራን ሳይመርጡ መስራታቸው ኢኮኖሚያዊ አቅማቸውን ከማሳደግ ባለፈ ለሌሎች ወጣቶች የስራ ዕድል መፍጠር መቻላቸውን በማህበር የተደራጁ ወጣቶች ተናገሩ።
ሀዋሳ፡ ግንቦት 10/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) ስራን ሳይመርጡ ለፍቶ ገቢ ማግኘትን ባህል በማድረጋቸው ኢኮኖሚያዊ አቅማቸውን /ከማሳደግ ባለፈ ለሌሎች ወጣቶች የስራ ዕድል መፍጠር መቻላቸውን በወልቂጤ ከተማ በማህበር የተደራጁ ወጣቶች ተናገሩ።
በበጀት ዓመቱ እስከ አሁን ለ27 ኢንተርፕራይዞች ኢኮኖሚያዊ አቅማቸውን ለማሳደግ ድጋፍና ክትትል በማድረግ ቋሚና ጊዜያዊ የስራ እድል መፍጠር መቻሉን የከተማ አሰተዳደሩ የስራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ጽ /ቤት አስታወቋል ።
በወልቂጤ ከተማ አሰተዳደር የጉብሬ ክፍለ ከተማ ትንሳኤ የጣውላ ውጤቶች አምራች ማህበር በ2009 ዓ.ም በአነስተኛ ካፒታል ስራ መጀመሩን ያስታወሰው የማህበሩ ሰብሳቢ ወጣት አለማየሁ ገብሩ በአሁኑ ወቅት በዘመናዊ ማሽን ጭምር በመታገዝ ጥራት ያለው የተለያዩ የጣውላ ምርቶችን በማምረት ውጤታማ ስራ እየሰሩ መሆናቸውን ተናግሯል።
ስራን ሳይመርጡ ለፍቶ ገቢ ማግኘትን ባህል በማድረጋቸው ኢኮኖሚያዊ አቅማቸውን ከማሳደግም ባለፈ ለሌሎች ወጣቶች የስራ ዕድል መፍጠር ችለናል ያለው ሰብሳቢው ስራ ስጀምር ጥቃቅንና አነሰተኛ ማህበር ከነበረበት በአሁኑ ወቅት ወደ ከፍተኛ ደረጃ መሸጋገራቸውን ገልጿል።
ማህበሩ በአራት አባላት የተመሰረተ ሲሆን በአሁን ላይ ከ27 በላይ ስራ አጥ ወጣቶች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ ዕድል መፍጠራቸውን የጠቀሰው ሰብሳቢው ከተማ አስተዳደሩ የመስሪያ ቦታ ማመቻቸቱን አብራርቷል።
ወጣቶች ጊዜያቸው አልባሌ ቦታ ከማሳለፍ ይልቅ ጉልበታቸውንና ዕውቀታቸውን ስራ ላይ ማዋል ከቻሉ ለውጥ ሩቅ አይደለም ያለው ወጣቱ ዓላማና የሰራ ተነሳሽነት ካለ ከምንም በመነሳት ህይወትን መለወጥ እንደሚቻል ምክሩን ለግሷል ።
ወጣት ጅላሉ ሻሚል እና ሌሎች የማህበሩ አባላት ከዩንቨርሲት እንደተመረቁ ከጠባቂነት ይልቅ መንግስት ባመቻቸላቸው ድጋፍ ፏፏቴ ብረታ ብረትና የቢሮ ዕቃዎች ማህበር በመመስረት ወደ ስራ መግባታቸውን አውስቶ በአሁኑ ወቅት ከሁለት ሚልዮን ብር በላይ ካፒታል ማስመዝገባቸውን ገልፆል።
ማህበሩ ምርታቸውን በጥራት በመስራት በከተማው በሚገኙ ድርጅቶች ተመራጭ መሆን መቻላቸውን ተናግሯል።
በማህበሩ በቋሚነት የስራ ዕድል ከተፈጠረላቸው ወጣቶች መካከል ወጣት ዮሐንስ ያሲን እና ሹምዬ ቀለብ በሰጡት አሰተያየት ከዚህ ቀደም ቋሚ ስራ እንዳልነበራቸው ጠቁመው በማህበሩ ውስጥ ተቀጥረው የመስራት ዕድል በማግኘታቸው ቤተሰባቸውን በአግባቡ ከመምራት ባለፈ የሙያ ባለቤት የመሆን ዕድል እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል።
በወልቂጤ ከተማ አሰተዳደር የስራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ጽ /ቤት ሃላፊ ተወካይ አቶ ኢብራህም መሀመድ እንዳሉት የስራ ዕድል ለመፍጠር ወጣቶች ልዩ ትኩረት ከተሰጠባቸው መስኮች መካከል እንደ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ተኪ ምርቶችንና ቴክኖሎጂዎችን በማምረት ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን ለመቀነስና የውጪ ምንዛሬን ለማስቀረት እየተሰራ ይገኛል፡፡
በዚህም በአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ ደረጃ ያሉ ማህበራት ቴክኖሎጂ ላይ በማተኮር ለግብርና ስራ የሚውሉ ማሽኖችንና የእንሰት መፋቂያ ማሽን በማምረት በበጀት ዓመቱ ከ 2 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ማግኘት መቻሉን ተናግረዋል ፡፡
በ2018 በጀት ዓመት የስራ ልየታ በማድግ ከ11 ሺህ 7 መቶ በላይ ስራ አጥ ወጣቶች በማህበር በማደራጀት እና በከተማ አስተዳደሩ በሚገኙ መንግስታዊና መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ እድል መፈጠሩን አቶ ኢብራህም ተናግረዋል፡፡
እስከ አሁን ለ 27 ኢንተርፕራይዞች ኢኮኖሚያዊ አቅማቸውን ለማሳደግ ድጋፍና ክትትል በማድረግ የስራ እድል መፈጠሩን የጠቀሱት ተወካዩ ለ11 ማህበራት ከ5 ሚሊዮን 9 መቶ ሺህ ብር በላይ ከተዘዋዋሪ ፈንድ በጀት በተለይም የምግም ዋስትናን የሚያረጋግጡ ትኩረት መስኮች እንደ ከብት እርባታ፣ ወተትና የዶሮ እርባታ ለተሰማሩ ወጣቶች መሰራጨቱን ተናግረዋል፡፡
ዘጋቢ፡ ተዘራ በቀለ – ከወልቂጤ ጣቢያችን

More Stories
በተለያዩ መስኮች የተመዘገቡ ድሎችን ይበልጥ ለማሳደግ የህዝቡ ድጋፍ በምርጫ መረጋገጥ አለበት – ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር)
ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) በተገኙበት በኮንታ ዞን የብልጽግና ፓርቲ የይምረጡኝ ቅስቀሳ እና ህዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ እየተካሄደ ነው
ህብር ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የምርጫ ማኒፌስቶ፣ የዕጩ ማስተዋወቂያ እንዲሁም የምርጫ ቅስቀሳ ፕሮግራም በጎፋ ዞን ሳውላ ከተማ አካሄደ