ኦርቢስ ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ ጥራት ያለው የአይን ህክምና በሀገሪቱ ተደራሽ ለማድረግ በትኩረት እየሰራ መሆኑ ተገለፀ

በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ የንግስት እሌኒ መሐመድ መታሰቢያ ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ከኦርቢስ ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር

የህፃናት የዓይን ህክምና አገልግሎት በሆስፒታሉ አስጀምሯል።

ኦርቢስ ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ ላለፉት 27 አመታት በተለያዩ አካባቢዎች የተለያዩ ስራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል ያሉት የኦርቢስ ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ ካንትሪ ዳይሬክተር ዶክተር አለማየሁ ሲሳይ፤ በተለይም የአይን ሞራ ግርዶሽ ችግር እና በመነጽር የሚስተካከሉ የእይታ ችግሮች በዋናነት ምላሽ እንዲያገኙ እየተሰራ ነው ብለዋል።

ኦርቢስ ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ የአምስት አመት ስትራቴጂክ እቅድ በማውጣት፣ ትራኮማ የተባለውን የአይን በሽታ ከሀገሪቱ ለማጥፋትና ማህበረሰቡ የአይን ጤናውን በተገቢው እንዲጠብቅ የአቅም ግንባታ ስልጠና እየሰጠ እንደሆነም አንስተዋል።

ህፃናት ለዓይነስውርነት ተጋላጭ እንዳይሆኑ፣ የህፃናት የአይን ህክምናን ማደራጀትና መከታተል የድርጅቱ ዋና ተልእኮ እንደሆነም አክለዋል።

ማህበረሰቡም የልጆቻቸውን የዓይን ምርመራ በማድረግ ድጋፍና ክትትል እንዲያደርጉ ዶ/ር አለማየሁ አሳስበዋል።

ዶክተር ዳዊት ስዩም የኦርቢስ ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ ካንትሪ ምክትል ዳይሬክተር እንደገለጹት ድርጅቱ በክልሉ የአይን ህክምናን መንስኤዎች ላይ በአይን ሞራ ግርዶሽ፣ ትራኮማ እና የእይታ ችግሮች ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

ከንግስት እሌኒ መሀመድ መታሰቢያ ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ጋር በመነጋገር በሆስፒታሉ የህጻናት የአይን ህክምና ማዕከል አስፈላጊ መሆኑን በመተማመን ዘመናዊ የህክምና መሳሪያዎችን በማደራጀት ማዕከሉ መከፈቱን ጠቁመዋል።

የማዕከሉ መከፈትም ከዚህ ቀደም ይስተዋሉ የነበሩ ችግሮችን የሚፈታና ለህጻናት በቴክኖሎጂ በተደገፈ መልኩ አገልግሎት እንደሚሰጥም ካንትሪ ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

የአይን ስውርነት ችግርን እስከ 80 ከመቶ መከላከል እንደሚቻል የተናገሩት ካንትሪ ዳይሬክተሩ፤ ህብረተሰቡ ህክምናውን መከታተልና ልጆችን በተገቢው ህክምና እንዲያገኙ ማድረግ እንደሚገባም ተገልጿል።

በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ የንግስት እሌኒ መሐመድ መታሰቢያ ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ቺፍ ኢክስክዩቲፍ ዳይሬክተር ዶ/ር ይድነቃቸው ደዳቸው በበኩላቸው፤ በሆስፒታሉ ከዚህ ቀደም የህፃናት ህክምና ከአዋቂዎች ህክምና ጋር ይሰጥ እንደነበር ገልጸው አሁን ላይ ግን ለህፃናት በሚመች መልኩ ከኦርቢስ ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር በዘመናዊ የህክምና መሳሪያ ተደራጅተው ስራ መጀመሩ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን አንስተዋል።

ሆስፒታሉ በርካታ የህክምና አገልግሎቶችን በስፔሻሊስት ሀኪሞች እየሰጠ መሆኑን የተናገሩት ዶክተር ይድነቃቸው፤ የህፃናት የአይን ህክምና መከፈት የማህበረሰቡን ችግር የሚፈታ እንደሆነም ጠቁመዋል።

በሆስፒታሉ የተጀመረው የህፃናት የአይን ህክምና የሆስፒታሉን የአገልግሎት ጥራት ከማሻሻልም አልፎ የማህበረሰቡን እንግልትና ወጪ የሚቀንስ በመሆኑ ማህበረሰቡ ድጋፍ እንዲያደርግም ዶክተር ይድነቃቸው ጥሪ አቅርበዋል።

በማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይ የኦርቢስ ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ የስራ ኃላፊዎች፣ የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዳዊት ሃዬሶ (ዶ/ር) እና የሀድያ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ ዶክተር ደሳለኝ ሽጉጤ(ዶ/ር) እንዲሁም የሆስፒታሉ የማኔጅመንት አባላት ተገኝተዋል።

ዘጋቢ፡ በየነ ሰላሙ – ከሆሳዕና ጣቢያችን