ብልጽግና ፓርቲ የማህበረሰቡ ችግር የሚቀርፉ ፕሮጀክቶችን ገንብቶ በማጠናቀቅ በውጤታማነት ለአገልግሎት እያበቃ ነው – ዶ/ር መሀመድ ኑርዬ

ብልጽግና ፓርቲ የማህበረሰቡ ችግር የሚቀርፉ ፕሮጀክቶችን ገንብቶ በማጠናቀቅ በውጤታማነት ለአገልግሎት እያበቃ ነው – ዶ/ር መሀመድ ኑርዬ

ብልጽግና ፓርቲ የማህበረሰቡ ችግር የሚቀርፉ ፕሮጀክቶችን ገንብቶ በማጠናቀቅ በውጤታማነት ለአገልግሎት እያበቃ ነው ሲሉ በምክትል ርእሰ መስተዳደር ማእረግ የመሰረተ ልማት ክላስተር አስተባባሪና የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር መሀመድ ኑርዬ ተናገሩ።

በየም ዞን ከ43 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸው የጤና ጣቢያ ማስፋፊያ፣ የመንገድና የድልድይ ግንባታ ፕሮጀክቶች ተመርቀው በዛሬው ዕለት ለአገልግሎት ክፍት ሆነዋል።

በምረቃ መርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት በምክትል ርእሰ መስተዳደር ማእረግ የመሰረተ ልማት ክላስተር አስተባባሪና የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር መሀመድ ኑርዬ፤ የመደመር እሳቤ የሚከተለው ብልጽግና ፓርቲ የማህበረሰቡን ችግር የሚቀርፉ ፕሮጀክቶችን ገንብቶ በማጠናቀቅ ለአገልግሎት ማብቃት ባህሉ እያደረገ ነው።

በየም ዞን ከሾሞመቴሎ – ቶሽኬማ የተገነባው ደረጃውን የጠበቀ የጠጠር መንገድ፣ የቶባና ፎፋ ወረዳዎችን የሚያገናኘው የአዘዋ ድልድይ እንዲሁም የሰምናማ ጤና ጣቢያ ማስፋፊያ ግንባታ ለአገልግሎት ከፍት መደረጋቸው ማሳያ ነው ብለው ይህም ፓርቲው ለሰብአዊ ብልጽግና እና ለፍትሃዊ የመሰረተ ልማት ተደራሽነት ተኩረት እንደሚሰጥ ገልጸዋል።

እነዚህ መሰረተ ልማቶች የህብረተሰቡ የልማት ክፍተቶችን የቀረፉ እና ማህበራዊ ብልጽግናን ያረጋገጡ ስለመሆናቸው የገለጹት ዶ/ር መሀመድ፤ በመደመር እሳቤ በየዘርፉ ብልጽግና ለማረጋገጥ የማህበረሰቡ ዘላቂነት ያለው ድጋፍ ወሳኝ እንደሆነም አስገንዝበዋል።

የተመረቁ ፕሮጀክቶችን በጥንቃቄ በመጠቀም ዘላቂነት እንዲኖራቸው ማድረግ ከማህበረሰቡ እንደሚጠበቅም አስረድተዋል።

የየም ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሽመልስ እጅጉ እነዚህ ክትትል ተደርጎባቸው የተመረቁ የማህበራዊ መሰረተ ልማት ፕሮጀክቶችን ጨምሮ በፓርቲው መሪነት የተተገበሩና እውን የሆኑ በርካታ የልማት ትሩፋቶች የዞኑን ማህበረሰብ ተጠቃሚ አድርገዋል ብለዋል።

በተለይም ከ43 ሚሊየን 343 ሺህ 575 ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸው የተመረቁ እነዚህ የማህበራዊ መሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ጤናን ከማስጠበቅ ባለፈ የቱሪዝም ኮሪደር በማስተሳሰሩ ላይ ሚናቸው ከፍተኛ ነው ሲሉም ተደምጠዋል።

ብልጽግና ቃል ከመግባት ባለፈ ሪቫን እየቆረጠ ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማስቀጠል ቁረጠኛ መሆኑን ያመላክታል ያሉት ዋና አስተዳዳሪው ይህንኑ ተግባር ለማስቀጠል የሁሉም ድጋፍና ተሳትፎ አስፈላጊ ስለመሆኑ አመላክተዋል።

የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ፋሲካ አለሙ በበኩላቸው ፓርቲው የጤናን መሰረታዊነት ተረድቶ በትኩረት በመስራቱ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት ተችሏል ብለዋል።

በእለቱ የማስፋፊያ ግንባታው ለተጠናቀቀው ለሰምናማ ጤና ጣቢያ ቢሮ ለመድሃኒት ግዢ የሚውል 4መቶ ሺህ ብር ድጋፍ እንደሚያደርግም ገልጸዋል።

የተመረቁ ፕሮጀክቶች ተጠቃሚ የሆኑ የፎፋ ወረዳ ነዋሪዎች በሰጡት አስተያየት ቀደም ሲል ለዘርፈ ብዙ ችግር ይዳረጉ እንደነበር አስታውሰው አሁን ላይ ፕሮጀክቶቹ ተገንብተው በመጠናቀቃቸው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እያገኙባቸው እንደሆነ ተናግረዋል።

በፓርቲው መሪነት መሰል ፕሮጀክቶች ተጠናቀው መመረቃቸው የማህበረሰቡን ችግር በመረዳት ዘላቂ መፍትሄ መስጠቱ እንዳስደሰታቸው የገለጹት ነዋሪዎቹ በቀጣይም ከፓርቲው ጎን ሆነው እንደሚደግፉም አመላክተዋል።

በምረቃ ስነሥርዓቱ ላይ በብልጽግና ፓርቲ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የፖለቲካ ርዕዮተዓለምና አቅም ግንባታ ዘርፍ ሃላፊ አቶ ይሁን አሰፋ እና የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መንገዶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢ/ር ምስጋና ማቲዎስን ጨምሮ ከክልል፣ ከዞንና ወረዳ የተውጣጡ አመራሮች እንዲሁም የአካባቢው ነዋሪዎች ተሳትፈዋል።

ዘጋቢ፡ አማን ቢካ – ከወልቂጤ ጣቢያችን