የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር የምርጥ ዘር ብዜት ስራን በራስ አቅም ተደራሽ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምርጥ ዘር ድርጅት አስታወቀ
በተያዘዉ የበልግ እርሻ ወቅት ከ11 ሺ ኩንታል በላይ የተለያዩ ምርጥ ዘሮችን ለክልሉ ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑም ተመላክቷል፡፡
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምርጥ ዘር ድርጅት ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ብርሃኑ ግዛዉ፤ የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ጥሩ ምርት የሚሰጡ የዘር ብዜቶች በራስ አቅም ማምረት ስለሚገባ ድርጅቱ ለዘር ብዜት አመቺ የሆኑ ስነ-ምህዳር ያላቸዉ ዞኖችን በመለየት የብዜት ስራዎችን እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ከዚህ ቀደም በአሪ ዞን ደቡብ አሪ ወረዳ ጨለጎድ ቀበሌ አርሶ አደሩን በኩታ ገጠም በማስተሳሰር ቢኤች 140 የበቆሎ ምርጥ ዘር በማምረት ዉጤታማ መሆናቸዉን የገለፁት ስራ አስኪያጁ፤ ዘንድሮ በዞኑ ባካ ዳዉላ ወረዳ በጌዛ ቀበሌ ላይ በተቋማት ማሳ ቢኤች 661 የበቆሎ የምርጥ ዘር እየለማ ነዉ ብለዋል፡፡
አክለዉም የዘር ብዜት ስራ አርሶ አደሩንም ሆነ ተቋማት ቴክኖሎጂን በቅርበት እንዲያዉቁና የተሻለ ገቢ እንዲያገኙ ያስችላቸዋል ብለዉ፤ በተያዘዉ የምርት ዘመን ከ500 ሄክታር መሬት በላይ የተለያዩ ምርጥ ዘሮችን በማልማት ከ11 ሺ ኩንታል በላይ ምርጥ ዘር ለክልሉ ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑንም አመላክተዋል፡፡
የአሪ ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ጉራልቅ ይዥማልቅ፤ ምርታማነትን ከሚያሳድጉ የግብርና ቴክኖሎጂዎች አንዱ ምርጥ ዘር በመሆኑ ከዚህ ቀደም የነበሩ የምርጥ ዘር አቅርቦት ችግሮችን ለመቅረፍ ከክልሉ ጋር በጋራ በመሆን የተለያዩ የምርጥ ዘር ብዜት ስራዎች ሲሰሩ መቆየታቸዉን ገልፀዉ፤ በተያዘዉ የበልግ እርሻ ወቅትም ለማምረት ከታቀደዉ 17 ሄክታር የበቆሎ ምርጥ ዘር ብዜት 15.5 ሄክታሩ በቢኤች 661 እና በቢኤች 546 የበቆሎ የምርጥ ዘር ብዜት መሸፈኑን ተናግረዋል፡፡
በአሪ ዞን ግብርና መምሪያ የዘር ብዜት ባለሙያ አቶ ጣሰዉ አሟልቴ በበኩላችዉ፤ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ለአርሶ አደሩ የግንዛቤ ትምህርት በመስጠት ከመሬት ዝግጅት ጀምሮ የበሽታ መከላከልና አረም ቁጥጥር ስራዎች እንዲሰሩ አስፈላጊዉን የድጋፍና ክትትል ስራዎችን እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በአሪ ዞን ባካ ዳዉላ አሪ ወረዳ የየትነበርሽ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ምክትል ርዕሰ መምህር መለሰ አደይ፤ የምርጥ ዘር ብዜት በትምህርት ቤት ቅጥር ግቢ ዉስጥ መካሄዱ አብዛኛዉ ተማሪ የአርሶ አደር ልጅ በመሆኑ የወንዴና የሴቴ ዘር እንዴት እንደሚዘራ ያገኘዉን ግንዛቤ ለቤተሰቦቹ የእዉቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ከማድረጉ ባለፈ የትምህርት ቤቱን የዉስጥ ገቢ ያሳድጋል ብለዋል፡፡
በበቆሎ ምርጥ ዘር ብዜት ከተሰማሩ መካከል አርሶ አደር ጋርሾ ተሰማ በላይነሽ ኦይካ መካከል አ ከባለሙያ ባገኙት ግንዛቤ መሰረት በቡቃያ ደረጃ ያለዉ ምርት ተስፋ ሰጪ በመሆኑ ወደ ፊት የተሻለ ምርት በማግኘት ለሌሎችም አርአያ እንደሚሆኑ ተናግረዋል፡፡
ዘጋቢ፡ በናወርቅ መንግስቱ – ከጂንካ ጣቢያችን

More Stories
በበልግ አዝመራ ከሚከናወኑ የግብርና ስራዎች ከ70 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት ታቅዷል – አቶ ማስረሻ በላቸው
የመንግሥትን የልማት ክፍተቶችን ለመሙላት የሚሰሩ የማህበረሰብ ልማት ድርጅቶች የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት በተሻለ ለማረጋገጥ በቅንጅት ሊሰሩ ይገባል – አምባሳደር ፍጹም አረጋ
7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሠላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሆሳዕና ከተማ ያነጋገርናቸው አንዳንድ የህብረተሰብ ክፍሎች ተናገሩ