በበልግ አዝመራ ከሚከናወኑ የግብርና ስራዎች ከ70 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት ታቅዷል – አቶ ማስረሻ በላቸው

በበልግ አዝመራ ከሚከናወኑ የግብርና ስራዎች ከ70 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት ታቅዷል – አቶ ማስረሻ በላቸው

በበልግ አዝመራ ከሚከናወኑ የግብርና ስራዎች ከ70 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው ገለጹ።

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው ወቅታዊ የበልግ አዝመራ ስራን በተመለከተ መግለጫ ሰጥተዋል።

አዝመራው ሲጀመር ፆም የሚያድር መሬት እንዳይኖር ከባለድርሻ አካላት ጋር በመወያየትና በመስማማት ወደ ስራ መገባቱን ገልጸዋል።

በዚህም በበልግ አዝመራ ከ415 ሺህ ሄክታር በላይ ማሣን በዋና ዋና ሰብሎች በመሸፈን ከ16 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

እስካሁን ከ422 ሺህ ሄክታር በላይ ማሣ በዘር መሸፈኑን የተናገሩት አቶ ማስረሻ፤ ከ119 ሺህ ሄክታር በላዩ መሬት በኩታ-ገጠም የአስተራረስ ዘዴ መከናወኑን አስታውቀዋል።

ከዚህም ባሻገር ለኤክስፖርት ምርቶች ልማትም ትኩረት መሰጠቱን ጠቁመው፤ ከ42 ሺህ 900 ሄክታር በላይ መሬት በቅባት እህሎች ማለትም በማሾ፣ በሰሊጥ፣ በቦሎቄና በሌሎችም የምርት ዓይነቶች መልማቱን ተናግረዋል።

በሆርቲካልቸር ሰብሎችም እንዲሁ በበልግ አዝመራና በሁለተኛ ዙር የመስኖ ልማት ስራ ከ108 ሺህ ሄክታር በላይ ማሣን በማልማት ከ21 ነጥብ 2 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት ታቅዶ እስካሁን ባለው አፈፃፀም ከ105 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት መልማቱን አስታውቀዋል።

ከዚህም ባሻገር በፍራፍሬ ልማት ስራ በበልግ አዝመራ ከ50 ነጥብ 8 ሚሊየን በላይ ችግኞችን ለማዘጋጀት መታቀዱንና እስካሁንም ከ50 ነጥብ 6 ሚሊየን በላይ የተለያየ ዝርያ ያላቸው ችግኞች ተዘጋጅተው፤ ከ23 ነጥብ 6 ሚሊየን በላይ ችግኝ 9 ሺህ 522 ሄክታር በሚሆን ማሣ ላይ ተተክሏል ብለዋል።

ከዚህ ቀደም ምርት በመስጠት ላይ የነበረው የፍራፍሬ ምርት መጠን ከ94 ሺህ ሄክታር በላይ መሆኑን ጠቁመው፤ 19 ሚሊየን ኩንታል ምርት መገኘቱን አንስተዋል።

በእንሰት ልማት ስራ በኩል ከ38 ሺህ 700 ሄክታር በላይ የእንሰት ችግኝ ለመትከል ታቅዶ ከ38 ሺህ ሄክታር በላይ መከናወኑን ጠቁመዋል።

አሁን ላይ በክልሉ ከ134 ሺህ ሄክታር በላይ የእንሰት ማሣ እንዳለ የተናገሩት ኃላፊው፤ ከ40 ሺህ ሄክታር የእንሰት ማሣ ላይ በበልግ ወቅት 7 ሚሊየን ኩንታል ምርት ተገኝቷልም ብለዋል።

በጥቅሉ በበልግ አዝመራ በዋና ዋና ሰብሎች ወደ 16 ሚሊየን ኩንታል፣ ከበልግ ሆርቲካልቸርና ከሁለተኛ ዙር መስኖ ወደ 21 ነጥብ 2 ሚሊየን ኩንታል፣ ከፍራፍሬ 24 ሚሊየን ኩንታል፣ ከእንሰት ወደ 8 ነጥብ 8 ሚሊየን ኩንታል ከ70 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት እስከ ክረምት ባለው ጊዜ እንደሚገኝ ይጠበቃል ብለዋል።

ከ159 ሺህ ኩንታል በላይ ምርጥ ዘር እና ከ86 ሺህ ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ በዚህ አዝመራ ጥቅም ላይ ውለዋል ነው ያሉት።

ከዚህ ባለፈ ከ185 ሺህ ቶን በላይ ኮምፖስት እስካሁን ባለው መጠቀም መቻሉን አስረድተዋል።

ዘጋቢ፡ ዮሐንስ ክፍሌ – ከቦንጋ ጣቢያችን