የመንግሥትን የልማት ክፍተቶችን ለመሙላት የሚሰሩ የማህበረሰብ ልማት ድርጅቶች የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት በተሻለ ለማረጋገጥ በቅንጅት ሊሰሩ ይገባል – አምባሳደር ፍጹም አረጋ

የመንግሥትን የልማት ክፍተቶችን ለመሙላት የሚሰሩ የማህበረሰብ ልማት ድርጅቶች የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት በተሻለ ለማረጋገጥ በቅንጅት ሊሰሩ ይገባል – አምባሳደር ፍጹም አረጋ

ሀዋሳ፡ ግንቦት 07/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) የመንግሥትን የልማት ክፍተቶችን ለመሙላት የሚሰሩ የማህበረሰብ ልማት ድርጅቶች የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት በተሻለ ለማረጋገጥ በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ፍጹም አረጋ አሳሰቡ፡፡

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በደቡብ ኦሞ ዞን በበና ፀማይ ወረዳ በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ድጋፍ የተገነባው የቦሪ ቀበሌ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ከፍተኛ የመንግሥት ሥራ ኃላፊዎችና የሀይማኖት አባቶች በተገኙበት በድምቀት ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ተደርጓል።

በፕሮጀክቱ ምረቃ ላይ የተገኙት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ፍጹም አረጋ፤ በሀገራችን ኢትዮጵያ ከ8 ሺህ በላይ የማህበረሰብ ልማት ድርጅቶች ተመዝግበው የተለያዩ የልማት ሥራዎች እያከናወኑ መሆኑን ጠቁመው ከእነዚህ ልማት ሥራዎች በአርብቶ አደሩ አካባቢዎች የሚታየውን የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግሮችን በመገንዘብ ከመንግሥት ጎን በመሆን የህዝቡን የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በልዩ ትኩረት እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

አምባሳደር ፍጹም አክለውም፤ የመጠጥ ውሃ ፍለጋ ረጂም ኪሎ ሜትሮችን የሚጓዙ እናቶችና ሴት ልጆችን ስቃይ እንዲሁም የእንስሳት ሀብት ጤናማነትን ለመጠበቅ በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ልማት ፕሮጀክት የተደረገው የመጠጥ ውሃ ልማት ፕሮጀክት ግንባታ እጅግ የሚደነቅ በመሆኑ በሌሎችም ልማት ሥራዎች ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከፍተኛ አማካሪ አቶ አበራ እንደሻው በበኩላቸው፤ የመንግስትን የልማት ክፈተትን ለመሙላት በአርብቶ አደሩ አካባቢዎች በልማት አጋሮች እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት አበረታች መሆናቸውን አንስተው በጀት የሚጠይቁ የልማት ሥራዎችን ከመንግስት ጋር በጋራ ትብብርና በቅንጅት በመሥራት የህዝቡን ተጠቀሚነት በዘላቂነት ለማረጋገጥ መስራት እንደሚገባም ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የሶዶ ሀገረ ስብከት ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ደጀኔ ሂዶቶ በምረቃው መርሐ ግብር ባስተላለፉት መልዕክት፤ ቤተክርስቲያኗ ከሀይማኖት ተልዕኮዋ በተጨማሪ በሌሎችም ልማት ሥራዎች እየተሳተፈች መሆኑን ጠቁመው ከዚህም ውስጥ አንዱ የንጹህ መጠጥ ውሃ ሲሆን በአርብቶ አደሩ አካባቢ የሚታየውን የውሃ ችግር ለመቅረፍና ህዝቡን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያ የCRS(Catholic Relief Service) ተወካይ አቶ ዘመዴ ዘውዴና የካሪታስ ሶዶ አስተባባሪ ነፃነት ደምሴ (ዶ/ር) የCRS ድርጅት በአሜሪካ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ጳጳሳት የተቋቋመ ድርጅት ሆኖ በኢትዮጵያ የተለያዩ ማህበረሰብ አቀፍ ልማት ሥራዎችን እየሰራ መሆኑን አንስተው በተለይም አርብቶ አደሩን መሠረት ያደረጉ የመጠጥ ውሃ፣ የጤናና ሌሎችም ልማታዊ ተግባራትን በቁርጠኝነት እያከናወነ ያለ ድርጅት ነው ሲሉ ሀሳባቸውን ሰጥተዋል።

የደቡብ ኦሞ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ታደለ ጋያ፤ በአካባቢው ከዚህ ቀደም የነበረው የመጠጥ ውሃ ችግር ከፍተኛ መሆኑን በመግለጽ በዞኑ የሚታየውን የመጠጥ ውሃ ሽፋን ለማሳደግና የማህበረሰቡን የልማት ጥያቄ ምላሽ ለመሰጠት የሚያደርጉ የልማት ድርጅቶችን አመሰግነው በቀጣይ አርብቶ አደሩን ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችሉ ልማት ሥራዎች ለመሳተፍ ለሚፈልጉ አጋር ድርጅቶች በራንችን ክፈት ነው ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።

የአካባቢው ማህበረሰብም ከዚህ በፊት የመጠጥ ውሃ ችግር መኖሩን ገልጸው፤ በመንግሥትና በሀይማኖት ተቋሙ በኩል ለመቅረፍና የልማት ጥያቄ ለመመለስ የተደረገውን ጥረት አድንቀው በመጠጥ ውሃ መጀመሩ እንዳስደሰታቸው ተናግረዋል።

ይህ ፕሮጀክት በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የሶዶ ሀገረ ስብከት ካሪታስ ሶዶ አማካኝነት ከCRS በተገኘ 50 ሚሊዮን ብር በሚጠጋ ገንዘብ ድጋፍ የተገነባ ሲሆን ይህ የልማት ስራ 11 ሺህ 530 የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርግና ከ90 ሺህ በላይ ለሚሆኑ የቤት እንስሳት ውሃን የሚያቀርብ ነዉ ተብሏል።

ፕሮጀክቱ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘና 22 ኪሎ ዋት የፀሐይ ብርሃን ኃይል የሚያመነጭ ሰፊ የሶላር ሲስተም ዝርጋታ የተገጠመለት ሲሆን በተጨማሪም 100 ሜትር ኩብ የውሃ ማጠራቀሚያ ገንዳ 9 የውሃ ቦኖዎች፣ 6 የእንስሳት መጠጫ ገንዳዎችና በትምህርት ቤትና በጤና ተቋማት የመጸዳጃ ቤቶችን ያካተተ መሆኑ ተመላክቷል።

ዘጋቢ: ጄታ ታገሠ – ከጂንካ ጣቢያችን