በምርጫ ጊዜ የሚነሱ ችግሮችን በገለልተኝነትና በህግ አግባብ ብቻ ለመፍታት የፍትህ አካላት ሚና የላቀ መሆኑ ተጠቆመ
በምርጫ ህጎች ላይ ያተኮረ የአቅም ግንባታ ስልጠና በጎፋ ዞን ለባለድርሻ አካላት ተሰጥቷል፡፡
የጎፋ ዞን ፍትህ መምሪያ ኃላፊ አቶ ደመላሽ ብላተ ስልናውን ሲከፍቱ እንዳሉት፤ ምርጫ የአንድ አገር ዴሞክራሲ መገለጫና የአገረ መንግስት ግንባታ ምሰሶ ነው።
ከዚህ አንጻር የፍትህ ተቋማት ገለልተኝነት ወሳኝ መሆኑን አንስተው፤ ምርጫው ነጻና ፍትሐዊ እንዲሆን የፍትህ ተቋማትና የጸጥታ አካላት ቁርጠኝነት የጎላ ሚና አለው ሲሉ ገልጸዋል።
የምርጫ ሂደቱ በመራጩ ህዝብ ዘንድ ቅቡልነት እንዲኖረው የፍትህ ተቋማት ችግሮችን በህግ አግባብ ለመፍታት ስልጠናው ማስፈለጉን ገልጸዋል።
ስልጠናው በዋናነት በምርጫ ህጎች፣ በምርጫ ሂደት አፈፃፀም፣ በህግ ማስከበር ስርዓት እንዲሁም በተፎካካሪ ፓርቲዎች መብትና ግዴታዎች ላይ ያተኮረ መሆኑ ተጠቁሟል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ፍትህ ቢሮ የአቃቢያነ ህግ አስተዳደር ዋና ጉባኤ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ላማላ አብርሃም፤ ስልጠናው የፍትህ አካላት በምርጫ ሂደት ዉስጥ ያላቸውን ሚና በመገንዘብ የህግ መሠረትን ለማጠናከር ታስቦ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።
በየትኛውም የዴሞክራሲ ስርዓት ምርጫ መሠረታዊ መሆኑን የተናገሩት ኃላፊዉ ሂደቱን ነፃ፣ ፍትሃዊና ህጋዊነቱን የጠበቀ እንዲሆን መስራት ይገባል ብለዋል።
በምርጫ ጊዜ የሚነሱ ችግሮችን በገለልተኝነትና በህግ አግባብ ለመፍታት ፖሊስ፣ ፍርድ ቤቶች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ባለድርሻ አካላት ያሉ ህጎችን በመገንዘብ በትብብር መስራት እንደሚጠበቅባቸው አስረድተዋል።
ሰልጣኞች በእነዚህ ጉዳዮች ላይ በቂ ግንዛቤ እንዲያገኙ እና በክልሉ ፍትሃዊና ህጋዊ የምርጫ ሂደት እንዲጠናከር ስልጠናው እንደሚያግዝ ተገልጿል።
የስልጠናው ሰነድ በዞኑ ዓቃቤ ህግ የምርጫ ፎካል ፐርሰን በሆኑት አቶ ማስረሻ ሰለሞን ቀርቦ ውይይት እየተደረገ ነው።
ያነጋገርናቸው የስልጠናው ተሳታፊዎች ምርጫው ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ እንዲሁም ቅቡልነት ያለው እንዲሆን የድርሻቸውን እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።
ዘጋቢ፡ አይናለም ሰለሞን – ከሳውላ ጣቢያችን

More Stories
የመንግሥትን የልማት ክፍተቶችን ለመሙላት የሚሰሩ የማህበረሰብ ልማት ድርጅቶች የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት በተሻለ ለማረጋገጥ በቅንጅት ሊሰሩ ይገባል – አምባሳደር ፍጹም አረጋ
7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሠላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሆሳዕና ከተማ ያነጋገርናቸው አንዳንድ የህብረተሰብ ክፍሎች ተናገሩ
በኣሪ ዞን ሰሜን አሪ ወረዳ የራጺ ታዳጊ ማዘጋጃ ቤት የ24 ሰዓት የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ ሆነች