በጎፋ ዞን ሳውላ ከተማ የምግብ ዋስትና ፕሮጀክት እየተስተዋለ ያለውን ድህነት እና የስራ አጥነት ችግር ለመቅረፍ ያበረከተው አስተዋጽኦ የላቀ መሆኑ ተገለጸ
በከተማው 431 የሁለተኛ ዙር የከተማ ምግብ ዋስትና ፕሮጀክት ተጠቃሚዎች የምረቃ መርሃ ግብር ተከናውኗል።
የሣውላ ከተማ ከንቲባ አቶ በላይነህ ባህሩ በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፤ በከተማው እየተስተዋለ ያለውን ስር የሰደደ ድህነትን ለመቀነስ በተደረገ ጥረት በርካታ የህብረተሰብ ክፍሎች በፕሮግራሙ ተሳታፊ ሆነው ኑሯቸውን ማሻሻል መቻላቸውን ጠቁመዋል።
ፕሮጀክቱ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ዜጎችን ተጠቃሚ በማድረግ ረገድ ውጤታማ ተግባራት ማከናወኑን ገልጸዋል።
የከተማ አስተዳደሩ የመንግሥት ዋና ተጠሪ አቶ ከተማ ከበደ፤ በፕሮግራሙ ታቅፈው የተመረቁ ዜጎች በህብረት ሥራ ማህበራት በመደራጀት ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸው ይበልጥ እየተጠናከረ እንዲመጣ ይሰራል ብለዋል
በቀጣይ ራሳቸውን ከመቻል አልፈው ለሌሎች ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር እንዲችሉ የባለድርሻ አካላት ሚና የላቀ ስለመሆኑን አስረድተዋል።
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የከተማው ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፍጹም ጳውሎስ፤ ስር በሰደደ ድህነት ውስጥ የሚኖሩ ወገኖች የምግብ ዋስትናቸውን በማረጋገጥ ለከተማዋ ዕድገት የራሳቸውን አሻራ እንዲያሳርፉ ማስቻል የፕሮጀክቱ ዓላማ መሆኑን ገልፀዋል።
የከተሞች ምግብ ዋስትና ፕሮጀክት በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ዜጎች ከተረጂነት አስተሳሰብ ወጥተው ወደ ምርታማነት መቀየርን የሰነቀ ፕሮጀክት መሆኑን ተናግረዋል።
የከተማ ልማታዊ ሴፍትኔት ፕሮግራም የከተማውን ገጽታ በመቀየር ጽዱ እና ማራኪ ከማድረግ ባሻገር የሥራና የቁጠባ ባሕልን ለማዳበር ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክትም ገልጸዋል።
የከተማው ልማታዊ ሴፍትኔት ሥራ ፕሮጀክት ዳይሬክተር አቶ ኢያሱ በላቸው፤ በ2ኛ ዙር በቤተሰብ የታቀፉ ዜጎች በጽዳትና ውበት፣ በአረንጓዴ አሻራ እና በሌሎች የልማት ስራዎች ላይ ተሰማርተው በኑሮአቸውና በከተማው ዕድገት ላይ ተጨባጭ ለውጥ ማስመዝገባቸውን ተናግረዋል።
በፕሮጀክቱ ታቅፈው ቆጥበው ኑሮአቸውን በማሻሻል ለውጥ ያስመዘገቡ ተመራቂዎች የዋንጫ፣ የምስክር ወረቀትና የገንዘብ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
ያነጋገርናቸው ተመራቂዎች በከተማ ልማታዊ ሴፍትኔት መርሃ ግብር ታቅፈው ወደ ተግባር በመግባታቸው ካለባቸው ስር የሰደደ የምግብ ዋስትና ችግር ተላቀው ቆጥበው ሀብት ማፍራት መጀመራቸውን ተናግረዋል።
በቀጣይም ራሳቸውን በመቻል እና ከተረጅነት በመላቀቅ በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ተሰማርተው እንደሚሰሩም ነው የገለጹት።
ዘጋቢ፡ አይናለም ሰለሞን – ከሳውላ ጣቢያችን

More Stories
የእናቶችንና ጨቅላ ህፃናትን ሞት ለመቀነስ በሚደረጉ ጥረቶች ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ ተገለፀ
የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርእሰ መስተዳደር (ዶ/ር ) እንዳሻው ጣሰው በተገኙበት በጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ምርቃትና የመሰረተ ድንጋይ የማስቀመጥ ስነ-ስረዓት እየተካሄደ ይገኛል
“ባለፉት 8 ዓመታት በሁሉም ዘርፍ የህዝብ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ የሚያስችሉ ስራዎች ተከናውነዋል” – ዶክተር ዲላሞ ኦቶሬ