“ባለፉት 8 ዓመታት በሁሉም ዘርፍ የህዝብ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ የሚያስችሉ ስራዎች ተከናውነዋል” – ዶክተር ዲላሞ ኦቶሬ
ሀዋሳ፡ ግንቦት 03/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) ባለፉት 8 ዓመታት በሁሉም ዘርፍ የህዝብ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ የሚያስችሉ ስራዎች መከናወናቸውን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የመንግስት ዋና ተጠሪ እና የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ ዶክተር ዲላሞ ኦቶሬ ገለጹ፡፡
ሀገራዊ ለውጡ እውን የሆነበትን 8ኛ ዓመት እና 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ በማስመልከት በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል፣ በየም ዞን ሳጃ ከተማ የድጋፍ ሰልፍና የምርጫ ቅስቀሳ ተካሄዷል።
በዕለቱ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ዶክተር ዲላሞ ኦቶሬ፤ የለውጡ መንግስት ባለፉት ስምንት ዓመታት ኢትዮጵያን ወደ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ማሸጋገር የሚያስችሉ ስኬታማ ተግባራትን ማከናወኑን ገልጸዋል፡፡
እንደ ኃላፊው ገለጻ፥ የመደመር ዕሳቤን መነሻ በማድረግ ጊዜውን የዋጁና ዘመን ተሻጋሪ የሆኑ ተግባራት በመከናወናቸው በየዘርፉ የላቀ ውጤት መመዝገቡን አመላክተዋል።
“ኢትዮጵያን ተምሳሌት የሆነች ሀገር ለማድረግ የገባነውን ቃል የምናድስበት ወቅት ላይ እንገኛለን” ያሉት ዶ/ር ዲላሞ፥ መንግስት ልዩነቶችን በማጥበብና ክፍተቶችን በመጠገን ለመጪው ትውልድ ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ በትኩረት እየሰራ መሆኑን አስረድተዋል።
በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊና በዲፕሎማሲ መስኮች የተመዘገቡ ውጤቶች በአፍሪካም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ በአብነት የሚጠቀሱ መሆናቸውን የገለጹት ኃላፊው፥ ከዕዳ ወደ ምንዳ የተሸጋገረ ሀገር በቀል እውቀትን መሰረት ያደረገ የኢኮኖሚ አመራር በመከተል፣ እምቅ አቅሞችን ወደ ውጤት በመቀየር የሚበረታታ የኢኮኖሚ ስርዓት ተፈጥሯል ብለዋል።
የምግብ ሉዓላዊነት ለመማረጋገጥ በተሰራ ስራ ድህነትን ለመቀነስና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እየተደረገ ያለው ጥረት ተስፋ ሰጪ ውጤት እያመጣ መሆኑን ጠቁመው፥ የአምራችና የኢንዱስትሪ ዘርፉን በማነቃቃት የውጭ ምርቶችን የሚተኩ(ተኪ ምርት) የሀገር ውስጥ ምርቶችን በስፋት ለማምረት ውጤታማ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ከተሞችን ውብና ዘመናዊነት የተላበሱ ለነዋሪዎች ምቹ ለማድረግ የተጀመሩ የልማት ስራዎች ከፍተኛ ለውጥ እያስመዘገቡ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በመጨረሻም መጪው ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ፣ ነፃ፣ ዲሞክራሲያዊና ፍትሃዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ መላው ህዝብ የበኩሉን ዜጋዊ ኃላፊነት እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ፡ ብርሃኑ ማሞ – ከወልቂጤ ጣቢያችን

More Stories
ወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የእርስ በርስ ግንኙነትና አንድነትን የሚያጠናክር ተግባር መሆኑ ተገለጸ
በክልሉ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ የተጀመሩ ተግባራት ተጠናክረው መቀጠል አለባቸዉ – ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ
የሕዝባችንን የልማት ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ የመመለስና ሜጋ ፕሮጀክቶችን በፍጥነት የማጠናቀቅ ቁርጠኝነታችንን አጠናክረን እንቀጥላለን-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)