የቀቤና ብሔረሰብን ባህል፣ ታሪክና ቋንቋ ለማሳደግ እና ትዉልድ ተሻጋሪ ለማድረግ የስነ-ጽሁፍ ስራዎች ያላቸዉ ሚና ከፍተኛ መሆኑን የቀቤና ልዩ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ መሐመድአሚን በደዊ ገለፁ

በልዩ ወረዳዉ “ባህላችን ለሁለንተናዊ ብልጽግናችን” በሚል የስነ-ጽሁፍ ምሽት በወልቂጤ ከተማ ተካሂዷል።

የቀቤና ልዩ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ መሐመድአሚን በደዊ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ ስነ-ጽሁፍ የሰዉ ልጅን ስሜት፣ ባህል፣ ታሪክና ቋንቋ ለማሳደግ ያለዉ ሚና ከፍተኛ ነዉ።

ስለሆነም የቀቤና ብሔረሰብ ባህል፣ ታሪክ፣ እሴቱንና ቋንቋዉን ከትዉልድ ወደ ትዉልድ ለማስተላለፍ በስነ-ጽሁፍ ስራዎች ላይ ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ ተናግረዋል።

ብልጽግና ፓርቲ ለሀገር በቀል እዉቀቶች ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል ያሉት ዋና አስተዳዳሪዉ፤ ወጣቱ ትዉልድ መጽሀፍትን በማንበብ ለሀገር ልማትና ሰላም የበኩሉን ሊወጣ ይገባል ብለዋል።

የቀቤና ልዩ ወረዳ ባህልና ቱሪዝም ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አብድልዋስ መሐመድ በበኩላቸዉ፤ ስነ- ጽሁፍ ለሰዉ ልጆች የእለት ተእለት እንቅስቃሴ ላይ ያለዉ ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።

በልዩ ወረዳዉ ለመጀመሪያ ጊዜ የተዘጋጀዉ ይህ የስነ-ጽሁፍ ምሽት አላማው አዲስና ነባር አማተር ቡድኖችና ወጣቶች ተሠጥኦዎቻቸውን እንዲያወጡ ለማድረግ መሆኑንም ገልጸዋል።

ጽ/ቤቱ የቀቤናን ባህል፣ ታሪክና ቋንቋን ለማሳደግ ብሎም አብሮነትን ለማስቀጠል እየሰራ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

የመርሃ-ግብሩ ታዳሚዎች በሰጡት አስተያየትም የስነ ጽሁፍ መድረክ መዘጋጀቱ ተሰጥኦ ያላቸዉ ወጣቶች የስነ-ጽሁፍ አቅማቸዉን ለማሳደግ ትልቅ ድጋፍ እንደሚያደርግላቸዉ በመግለፅ ተግባሩ ቀጣይነት እንዲኖረዉ በዘርፉ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባ ተናግረዋል።

በመድረኩ በቀቤንሲና ቋንቋ የተዘጋጀ “ኑ እንመካከር” ወይም Ammiyye Amaa’lamno የተሰኘ የገጣሚ ሙባረክ ሁሴን የግጥም መደብል የተመረቀ ሲሆን የተለያዩ የስነ-ጽሁፍ ስራዎችም ቀርበዋል።

ዘጋቢ፡ ሪያድ ሙህዲን – ከወልቂጤ ጣቢያችን