ከጂኦግራፊያዊ እስረኝነት ወደ ቀጣናዊ መሪነት

ከጂኦግራፊያዊ እስረኝነት ወደ ቀጣናዊ መሪነት

ኢትዮጵያ በታሪክ ማኅደር ስሟ ከቀይ ባሕርና ከዓለም አቀፍ የንግድ መተላለፊያ መስመሮች ጋር ተሳስሮ የቆየ ሀገር ናት። ይሁን እንጂ ባለፉት ሦስት አስርት ዓመታት ኢትዮጵያ “የየብስ እስረኛ” (Landlocked) ሆና እንድትቆይ መደረጓ፥ በልማቷ፣ በደኅንነቷና በሉዓላዊነቷ ላይ ትልቅ አደጋ ደቅኖ ቆይቷል። ዛሬ ላይ የባሕር በር ጥያቄ የፍላጎት ጉዳይ ሳይሆን የ130 ሚሊዮን ሕዝብ የህልውና እና የብሔራዊ ጥቅም ማረጋገጫ ሆኖ ብቅ ብሏል።

ኢትዮጵያ የታሪክ እና የሞራል ልዕልና ባለቤት ናት፤ ኢትዮጵያ የባሕር በር የነበራት ሀገር መሆኑ የታሪክ ድንገቴ ሳይሆን የተፈጥሮ ሀቅ ነው። ከአክሱም ስልጣኔ ጀምሮ የአዱሊስ ወደብ የዓለም የንግድ ማዕከል እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ያረጋግጣሉ። የባሕር በር ማጣት በሂደት የተከሰተ የታሪክ ስብራት እንጂ የሕግ ውጤት አይደለም።

በ1993ቱ የኤርትራ መገንጠል ሰበበ-ምክንያት፥ ኢትዮጵያ የባሕር በር አልባ እንድትሆን የተደረገው በወቅቱ በነበሩ የፖለቲካ ኃይሎች ስምምነት እንጂ፥ በሕዝብ ውሳኔ (Referendum) የታገዘ አልነበረም። ይህም ጥያቄው ዛሬም ድረስ የሞራል እና የታሪክ መሠረት እንዲኖረው አድርጎታል።

የኢኮኖሚ ደም ሥር እና የንግድ ተወዳዳሪነት

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ፈጣን እድገት ከሚያስመዘግቡ ሀገራት አንዷ ብትሆንም የባሕር በር ማጣት የኢኮኖሚዋን “ደም ሥር” እንደመቁረጥ ይቆጠራል። በሀገሪቷ ውስጥ ያለውን ፈጣን እድገት ተከትሎ፥ ለወደብ ኪራይና አገልግሎ በየዓመቱ ከ1.5 እስከ 2 ቢሊዮን ዶላር የምትከፍለው ክፍያ ለታዳጊ ኢኮኖሚ ትልቅ ሸክም ነው።

የንግድ መጠን በአሁኑ ወቅት በዓመት የምታንቀሳቅሰው 20 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ጭነት በ2030 ወደ 35 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ያድጋል ተብሎ ይገመታል። የራስ የባሕር በር አለመኖር የዋጋ ግሽበትን ከመጨመሩም በላይ፥ የውጭ ንግድ ተወዳዳሪነትን (Export Competitiveness) በእጅጉ ይጎዳል።

ጂኦ-ፖለቲካዊ እና ቀጣናዊ ደኅንነት

ቀይ ባሕር በዓመት ከ1 ትሪሊዮን ዶላር በላይ የንግድ ልውውጥ የሚያልፍበት ስትራቴጂካዊ መስመር ነው። እንዲህ ያለ ግዙፍ የሕዝብ ቁጥርና ወታደራዊ አቅም ያላት ሀገር ከዚህ ቀጠና መገለሏ ለቀጠናው ሰላም ዋስትና አይሆንም።

ኢትዮጵያ ካለችበት የጂኦ-ፖለቲካዊ እና ቀጣናዊ ደኅንነት አኳያ የባሕር ኃይል አስፈላጊነት አጠያያቂ አይደለም፤ የቀይ ባሕር ቀጠና ለባሕር ላይ ወንበዴነት፣ ለሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርና ለሽብርተኝነት የተጋለጠ ነው። ኢትዮጵያ ጠንካራ የባሕር ኃይል ኖሯት በንቁ ተሳትፎ መገኘቷ የዓለም አቀፍ የንግድ መስመሮችን ደኅንነት ለመጠበቅ አስተዋጽኦ ያበረክታል።

ከዚህ በተጓዳኝ በቀጠናው የጋራ ተጠቃሚነት (Win-Win Solution) እውን ለማድረግ ኢትዮጵያ በስፍራው መገኘት ለውሳኔ የሚቀርብ አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ጥያቄ የሌላውን ሉዓላዊነት በመጋፋት ላይ የተመሠረተ ሳይሆን፥ በልማት ሽርክና (Port-for-Equity) ወይም በሊዝ ስምምነት ላይ ያተኮረ ነው። ይህም ለጎረቤት ሀገራትም ትልቅ የኢኮኖሚ ዕድል ይፈጥራል፡፡

የሕግ እና የዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ አግባብ የኢትዮጵያን ፍላጎት በጽኑ የደገፈ ነው፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የባሕር ሕግ (UNCLOS) የየብስ እስረኛ ሀገራት ወደ ባሕር የመድረስ መብት እንዳላቸው ይደነግጋል። ኢትዮጵያ ይህንን መብቷን በሰላማዊ መንገድና በዲፕሎማሲያዊ ድርድር ለማስከበር የምታደርገው ጥረት ከዓለም አቀፍ መርሆዎች ጋር የተጣጣመ ነው።

ኢትዮጵያ “የመልክዓ-ምድር እስረኛ” ሆና የምትቀጥልበት ዘመን ሊያበቃ ይገባል። የባሕር በር ባለቤትነት ለሀገራችን ብልፅግና፣ ለሕዝባችን ክብር እና ለቀጣናው ዘላቂ ሰላም ወሳኝ ነው። ልክ እንደ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ሁሉ፣ የባሕር በር ባለቤትነትም የትውልድ አደራ እና የሉዓላዊነት መገለጫ ነው። ኢትዮጵያ በክብር ወደ ተፈጥሯዊ ቤቷ—ወደ ባሕር ዳርቻዋ—መመለሷ የታሪክ ግዴታ እንጂ ምርጫ አይደለም።

በዘላለም ተስፋዬ