በሀገሪቱ ያለውን የመሬት ሀብት በአግባቡ ማስተዳደር ከሁሉም አካል የሚጠበቅ ተግባር መሆኑ ተገለጸ

በሀገሪቱ ያለውን የመሬት ሀብት በአግባቡ ማስተዳደር ከሁሉም አካል የሚጠበቅ ተግባር መሆኑ ተገለጸ

ሀዋሳ፡ ግንቦት 01/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) በሀገሪቱ ያለውን የመሬት ሀብት በአግባቡ ማስተዳደር ከሁሉም አካል የሚጠበቅ ተግባር መሆኑን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ረዳት የመንግስት ተጠሪና የክልሉ ብልጽግና ፓርቲ ፖለቲካና ርዕዮተ ዓለም ዘርፍ ኃላፊ አቶ ንጋቱ ዳንሳ ገለጹ።

በደቡብ ኦሞ ዞን የማሌ ወረዳ ሁለተኛ ደረጃ የመሬት ልኬታ ማስጀመሪያ ፕሮግራም በተካሄደው መርሐ ግብር በመገኘት ነው አቶ ንጋቱ ይህንን የገለጹት።

መንግስት ገጠርንና ከተማን ትራንስፎርም ለማድረግ እየሠራ ሲሆን በዚህም የመሬት ሀብትን በአግባቡ መያዝና ማስተዳደር ብሎም ዕወቀት ላይ የተመሰረተ የኢኮኖሚ ባለቤት መሆን ይጠበቃል ብለዋል አቶ ንጋቱ።

የመሬት ልኬታው በሚፈለገው ልክ ተግባራዊ እንዲሆን ሁሉም ተባባሪ ሊሆን ይገባል ሲሉም አሳስበዋል።

የማሌ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አልጋጋ ባልንሴ፤ መሬት ትልቁ የኢኮኖሚ ሀብትና የኑሮ መሠረት ነው ብለዋል።

የመሬትን ሀብት በአግባቡ መጠቀምና ማስተዳደር ይጠበቃል ያሉት አስተዳዳሪው፤ በ2004 ዓ.ም የመጀመሪያ ዙር የመሬት ልኬት ሲደረግ ትክክለኛ መረጃ ተደራጅቶና ተሰንዶ አለመለካቱን አስታውሰው በሁለተኛው ዙሪ በሚካሄደው በቴክኖሎጂ የታገዘና አስፈላጊ ናቸው የተባሉ መረጃዎች ተደራጅተው ተግባራዊ ሊደረግ ይገባል ብለዋል።

አርሶ አደሩም ከመሬት የሚገኘውን ጥቅም በመገንዘብ ሰፊ መሬት ከመያዝ ይልቅ ሊያለማ የሚችለውን በአግባቡ በማስለካት የኢኮኖሚ ባለቤት መሆን አለበት ሲሉ አቶ አልጋጋ አሳስበዋል።

እንደ ወረዳ ከ35 ሺህ ሄክታር በላይ የሚታረስ መሬት እንዳለም ተገልጿል።

የደቡብ ኦሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ማዕከል ማሊኮ፤ መሬትን በአግባቡ በመያዝ አርሶ አደሩ ዘመናዊ አስተራረስና አመራረት ዘይቤን በመከተል ራሱ ተጠቃሚ ሆኖ አካባቢውን እንዲለውጥ ሀላፊነቱን ሊወጣ ይገባል ብለዋል።

እንደ ዞን ከ85 ሺህ በላይ በግብርና ሊለማ የሚችል የመሬት ሀብት መኖሩን በንግግራቸው የጠቀሱት ዋና አስተዳዳሪው፤ አርሶ አደሩ የመሬት ሀብቱን ከፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ጋር በማስተሳሰር ማስተዳደር እንደአለበት ተናግረዋል።

የተፈጥሮ ደን አካባቢዎችን መጠበቅና መንከባከብ የደን ሀብቱን ከመጠበቅ ባሻገር የሚከሰትን የተፈጥሮ ጎርፍ መከላከል ያስችላል ሲሉ ዋና አስተዳዳሪው አክለዋል።

ለአርሶ አደሩ በሚመቸው የባንክ ብድር በመጠቀም በመሬት ላይ በቂ ልማትን ተግባራ በማድረግ የኢኮኖሚ ባለቤት ሊሆን ይገባል ተብሏል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የመሬት አስተዳደር ቢሮ ምክትልና የመሬት አጠቃቀምና የጂኦ ስፓሻል ዘርፍ ኃላፊ ዮሴፍ ማሩ (ዶ/ር)፤ መሬት ውስንና ውድ የተፈጥሮ ሀብት ነው ብለዋል።

በዚህም ሀብቱን በአግባቡ ቆጥሮ መለየትና መንከባከ፣ ማስተዳደርና ለትውልዱ በዘላቂነት ማስተላለፍ ያስፈልጋል ብለዋል።

በክልል ደረጃ 65 ወረዳዎች እንዳሉ የጠቀሱት ሀላፊው ከእነዚህም ደቡብ ኦሞ ዞን ማሌ ወረዳ፣ ጌዴኦ ዞን ገደብ ወረዳና ወላይታ ዞን ቦሎሶ ሶሬ አደረጃጀቶች ይህ ስራ ተግባራዊ ሆኖ አርሶ አደሩ ከባንክ ሲስተም ጋር ትስስር ተፈጥሮ በመሬት ሀብት የኢኮኖሚ ባለቤት እንዲሆኑ ተወስኖ ወደ ተግባር መገባቱን ዶ/ር ዮሴፍ አብራርተዋል።

የአካባቢው ነዋሪዎችም መሬታቸውን በአግባቡ ለማስለካትና ከሀብቱ ተጠቃሚ ለመሆን እንደሚሠሩ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ዘጋቢ: ተመስገን አበራ – ከጃንካ ጣቢያችን