የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ባህልና ስፖርት ቢሮ የሀገሪቱን ቋንቋዎች ዲጂታላይዝ በማድረግ፣ ዘመኑን የሚመጥን የቋንቋ ልማት ማከናወን እንደሚገባ ገለፀ
ቢሮው ከፌደራል ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር፣ ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲና ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር በክልሉ የሚገኙ ቋንቋዎችን ዲጂታላይዝ ለማድረግ የመጀመሪያ ዙር ሥልጠና መስጠት ጀምሯል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ባህልና ስፖርት ቢሮ ምክትል ኃላፊና የባህል ልማት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ታሪኩ ኦይቻ፤ የሥልጠናውን ዓላማ ሀገራዊ ቋንቋዎችን በዲጂታል ቴክኖሎጂ መሰነድ፣ ማስተዋወቅና ማልማት መሆኑን አብራርተዋል።
ቋንቋዎችን በሀገር አቀፍና በዓለም አቀፍ የቴክኖሎጂ ቋት ውስጥ በማስገባት ሰዎች በቀላሉ እንዲያገኟቸው ለማድረግ ያለመ መሆኑንም አክለዋል።
ቋንቋ ብዝሃ ባህልን የያዘ በመሆኑ የቋንቋው ባለቤትና ሌላው ማህበረሰብ ሳይቸገሩ መረጃዎችን እንዲለዋወጡና ቋንቋውን ለዓለም ተደራሽ ለማድረግ እንደሚሰራም ተገልጿል።
በተጨማሪም ቋንቋ ማንነትን፣ እሴትንና ባህልን አቅፎ የያዘ በመሆኑ ከመግባቢያነት ባለፈ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እንዲኖረው እንዲሁም የትኛውም የዓለም ክፍል ቋንቋዎቹን በቀላሉ እንዲያውቃቸው፣ እንዲፈልጋቸውና ሳይቸገር ተርጉሞ እንዲጠቀምባቸው ለማስቻል ያለመ መሆኑ ተመላክቷል።
በመጀመሪያው ዙር በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የሥራ ክልል ውስጥ የሚገኙ የኮንሶ፣ ደራሼ፣ ጋሞ፣ የዛይሴ እና የግዲቾ ቋንቋዎችን ዲጂታላይዝ ለማድረግ ሥልጠናው መጀመሩን የገለጹት አቶ ታሪኩ፤ ሥራው ቀጣይነት እንደሚኖረውና በክልሉ የሚገኙ ሌሎች ቋንቋዎችንም ለማካተት እንደሚሠራ ተናግረዋል።
የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ መምህርና የፕሮጀክቱ መስራችና አስተባባሪ ሼካር ካማኑሪ(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ አሁን ያለው ዘመን የቴክኖሎጂ በመሆኑና ኢትዮጵያም “ዲጂታል ኢትዮጵያን” እውን ለማድረግ እየሰራች ባለችበት ወቅት የሀገር በቀል ቋንቋዎችን ዲጂታላይዝ ማድረግ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
ይህም የአፍ መፍቻ ቋንቋን ለማሳደግ፣ ባህልን ለመጠበቅ፣ ስለ ቋንቋዎች ያለውን የተዛባ አመለካከት ለመቅረፍና በማህበረሰቡ መካከል ጤናማ መስተጋብር ለመፍጠር እንደሚያግዝ ተናግረዋል።
የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ባህልና ቋንቋ ጥናት ተቋም ዳይሬክተር አቶ ታፈሰ ዋልኤ፤ ዩኒቨርሲቲው ቋንቋዎችን ከማልማት አንጻር የበኩሉን ሚና እየተወጣ መሆኑን ገልጸዋል።
ቋንቋዎችን ከማሽኖች ጋር ለማላመድና ሰዎች ያለ መምህር ወይም አስተርጓሚ እገዛ መማር እንዲችሉ እየተሰራ መሆኑንም አብራርተዋል።
ከሰልጣኞች መካከል ሳሙኤል ጎንደሬ (ዶ/ር)፣ አቶ ሠራዊት ወልዴ እና እንግዳ ኩሲያ፤ ሥልጠናው በቋንቋዎች ውስጥ ያሉ እሴቶችን ለማውጣትና ከዲጂታል ዘመኑ ጋር ለመራመድ ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው፤ በትጋት በመከታተል የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ዘጋቢ፡ አማሮ አርሳባ – ከአርባምንጭ ጣቢያችን

More Stories
የአርሰናል የድል ጉዞ እና የዌስትሃም ቁጭት!
በክልሉ የሚገኙ ነዋሪዎችን ሁለንተናዊ የልማት ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የሚያስችል ሥራ በትኩረት እየተሠራ እንደሚገኝ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ(ዶ/ር) ገለጹ
“በVAR ላይ እምነት የለኝም!” – ፔፕ ጋርዲዮላ